ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ሲዳማ ቡና ከ አዳማ ከተማ

በሌላኛው የ19ኛ ሳምንት ጨዋታ ሲዳማ አዳማን ያስተናግዳል።

ለሦስተኛ ተከታታይ ቀን የፕሪምየር ሊግ ጨዋታን የሚያስተናግደው የሀዋሳው ሰው ሰራሽ ሜዳ ነገ 09፡00 ላይ ሲዳማ ቡና እና አዳማ ከተማ ይገናኙበታል። ከጥር መገባደጃ በኋላ ሀዋሳ ላይ ጨዋታ ያላደረገው ሲዳማ ቡና ስድስት ከተሞችን ከተዟዟረ በኋላ ነው በሜዳው አዳማን የሚያስተናግደው። በነዚህ ጊዜያት አጥጋቢ የሚባል ነጥብ ባለመሰብሰቡም በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ወደ ፊት መራመድ አልቻለም። ከመሪው በስምንት ነጥብ ርቀው ሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠት ሲዳማዎች ነገ ውጤት ከቀናቸው ወደ ሁለት ከፍ የማለት ወይንም ወደ አራተኝነት የመንሸራተት አጋጣሚ ይኖራቸዋል። ጥሩ የማጥቃት ተሳትፎ ሲያደርግ ይታይ የነበረው የግራ መስመር ተከላካያቸው ሚሊዮን ሰለሞንን በጉዳት የማያሰልፉት ሲዳማዎች አበባየው ዮሃንስ እና ጫላ ተሺታን ደግሞ በተቃራኒው ከጉዳት መልስ ያገኛሉ።

ከአምስት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች እና ከቅዱስ ጊዮርጊሱ ሽንፈት ነኋላ ስሑል ሽረን በሰፊ ጎል በመርታት ወደ ድል የተመለሱት አዳማ ከተማዎች በሰንጠረዡ ከአስር ወደ አምስት ከፍ ማለትን በማለም ወደ ሀዋሳ አቅንተዋል። ዘንድሮም ወጥ ጉዞ ማድረግ የከበደው አዳማ የሽረው ድል የሚፈጥርለት መነሳሳት በቀላሉ የሚታይ ባይሆንም ከሜዳ ውጪ ያለው ደካማ ሪከርድ ሲታይ ደግሞ በሲዳማም ሊፈተን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። አዳማ አብዛኛውን የውድድር ጊዜ ከጉዳት ማገገም ያልቻለው መስመር ተከላካይ አንዳርጋቸው ይላቅ አና ቡልቻ ሹራን በጉዳት ፣ ግዙፉን የመሀል ተከላካይ ቴዎድሮስ በቀለን በህመም እንዲሁም ብዙአየው እንደሻዉን ደግሞ በቅጣት ምክንያት ሲያጣ በጊዮርጊሱ ጨዋታ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ያጣው ምኞት ደበበን ከቅጣት መልስ ያገኛል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ከ2002 የውድድር ዓመት ጀምሮ ሁለቱ ቡድኖች በ17 ጨዋታዎች ሲገናኙ 14 ግቦችን ያስቆጠረው ሲዳማ በሰባት ድሎች ቀዳሚ ሲሆን አዳማ ደግሞ 13 ግቦችን አስቆጥሮ አራት ድሎችን አሳክቷል ፤ ቀሪዎቹ ስድስት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ነበሩ።

– አዳማ ከተማ እስካሁን ከሜዳው ውጪ ካደረጋቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች መከላከያን በገጠመበት ጨዋታ ብቻ ነው ድል የቀናው። ከዛ ውጪ ሦስቴ ሲሸነፍ አምስቴ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

– ሲዳማ ሀዋሳ ላይ ዘጠኝ ጨዋታዎችን አድርጎ ስድስቱን በድል ሲወጣ በተቀሩት ሦስት ጨዋታዎችም ነጥብ መጋራት ቿሏል።

ዳኛ

– ዘንድሮ በዋና ዳኝነት ከተመደበባቸው ጨዋታዎች ውስጥ ሲዳማን ከሽረ አዳማን ደግሞ ከድሬዳዋ ያጫወተው ቢኒያም ወርቅአገኘሁ ይህን ጨዋታ ይመራዋል። ስድስት ጊዜ አራተኛ ዳኛ በመሆን ያገለግለው አርቢትሩ በአራት ጨዋታዎች 27 የማስጠንቀቂያ እና አንድ የቀይ ካርዶችን ሲመዝ ሁለት የፍፁም ቅጣት ምቶችን ሰጥቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

መሳይ አያኖ

ግሩም አሰፋ – ፈቱዲን ጀማል – ሰንደይ ሙቱኩ – ዳግም ንጉሴ

ወንድሜነህ ዓይናለም – ዮሴፍ ዮሃንስ – ግርማ በቀለ

ሐብታሙ ገዛኸኝ – መሀመድ ናስር – አዲስ ግደይ

አዳማ ከተማ (4-2-3-1)

ሮበርት ኦዶንካራ

ሱሉይማን ሰሚድ – ምኞት ደበበ – ተስፋዬ በቀለ – ሱለይማን መሀመድ

አዲስ ህንፃ – ኢስማኤል ሳንጋሪ

ኤፍሬም ዘካርያስ – ከነዓን ማርክነህ – በረከት ደስታ

ዳዋ ሆቴሳ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡