ሪፖርት | የሐብታሙ ገዛኸኝ ብቸኛ ግብ ሲዳማ ቡናን ዳግም ወደ ድል መልሶታል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 19ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ሲዳማ ቡና በሀዋሳ አርቲፊሻል ስታድየም አዳማ ከተማን አስተናግዶ 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት አሸንፏል።

በጨዋታው ላይ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ በተገኙበት እና የእለቱ ፌደራል ዳኛ ቢንያም ወርቅአገኝሁ በጥሩ ብቃት በመሩት ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ሲዳማ ቡናዎች ባለፈው ሳምንት ባህር ዳር ላይ 1-0 ከተሸነፈው ስብስብ ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖን በፍቅሩ ወዴሳ እንዲሁም ትርታዬ ደመቀን በወንድሜነህ ይይናለም ተክተው ነበር የገቡት። እንግዳው ቡድን አዳማ ከተማ በአንፃሩ ከባለፈው ሳምንት በሜዳዉ ስሑል ሽረን አስተናግዶ 4-1 ካሸነፈው ስብስብ በቅታት ምክኒያት ያልተጠቀመበትን ምኞት ደበበ በማስገባት ቴዎድሮስ በቀለን አሳርፈው ነበር ወደሜዳ የገቡት።

በመጀመሪያው አጋማሽ እንግዳው ቡድን በመሀል ሜዳው የሲዳማን ቅብብሎች በማቋረጥ እና ወደ መስመር በመጣል የተሻለ ተጭነው ሲጫወቱ ተስተውለዋል። 15ኛው ደቂቃ ላይ ከመሀል ወደ ቀኝ መስመር ከከንዓን ማርክነህ የተሻረለትን ኳስ ሱሌማን መሐመድ ወደ ሳጥን ይዞ ገብቶ የሞከረው ጥሩ የሚባል ሙከራ ነበር። በ20ኛው ደቂቃ ላይ ኢስማኤል ሳንጋሪ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ ግብ ጠባቂ ቀድሞ ሲያድንበት 25ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ በመስመር ለከነዓን ማርክነህ በግራ ጠርዝ ሳጥን ውስጥ አስገብቶ  የሰጠውን ኳስ ከነዓን ወደግብ መትቶ ግርማ በቀለ ተንሸራቶ ያዳነበት ሙከራዎችም ተጠቃሽ ነበሩ።

የአዳማ ከተማን የመስመር እንቅስቃሴ ለመገደብ በ30ኛው ደቂቃ ተጫዋች ለመቀየር የተገደዱት ሲዳማ ቡናዎች የከንዓን ማርክነህ እና በረከት ደስታን እንቅስቃሴ ለማቆም ዳግም ንጉሴን በማስወጣት ተስፉ ኤልያስን አስገብተው የግራ መስመር ተከላካዩን ግሩም አሰፋን ወደቀኝ በማምጣት በተወሰነ መልኩ የመስመር እንቅሰቃሴውን መቆጣጠር ችልዋል ።

ባለሜዳዎቹ በኩል በመልሶ ማጥቃት ከመሀል የሚገኙትን ኳሶች ለሐብታሙ ገዛኸኝ እና አዲስ ግደይ በማሻገር ነበር የማጥቃት እንቅስቃሴቻዉ የተመሰረተው። በሙከራ ደረጃ 6ኛ ደቂቃ ላይ ከወንድሜነህ ዓይናለም የተሻገረለትን ኳስ ሐብታሙ ገዛህኝ ከሳጥን ውጭ አክርሮ ቢመታውም ኢላማውን መጠበቅ ያልቻለው እንዲሁም ተመሳሳይ 16ኛ ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ከመሐመድ ናስር የተሻገረለትን ኳስ ወንድሜነህ ዓይናለም በግሩም ሁኔታ ወደግብ መትቶ ግብ ጠባቂ ያዳነበት ሌላው የሚጠቀስ ሙከራ ነው። 34ኛ ደቂቃ ላይ ወንድሜነህ ዓይናለም ያሻገረውን የማዕዘን መሐመድ ናስር በጭንቅላቱ ቢገጭም ሮበርት ኦዶንካራ በግሩም ሁኔታ ሲያድንበት 38ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ግደይ መሀል ለመሐል ያሾለከውን ኳስ ሐብታሙ ገዛኸኝ ከግብጣባቂው ጋር ተገናኝቶ ኦዶንካራ አውጥቶበታል። የተገኝውን የማዕዘን ምት ሲሻማም አዲስ ህንፃ ገጭቶት ለጥቂት ከራሱ ግብ ላይ ሊያስቆጥረው የነበረው በመጀመሪያው አጋማሽ የሚጠቀስ ሙከራ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ገና ከጅማሮው ሲዳማ ቡናዎች ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ከመሀል ሜዳ ኳስ የጀመሩት አዳማ ከተማዎች ወደኋላ የመለሱትን ኳስ ከምኞት ደበበ በመንጠቅ ወንድሜነህ ዓይናለም ከግብ ጠባቂ ጋር አገናኝቶ ያቀበለውን ኳስ ሐብታሙ ገዛኸኝ በሮበርት ኦዶንካራ አናት ላይ ከፍ በማድረግ ድንቅ ግብ አስቆጥሮ ባለሜዳዎቹን መሪ ማድረግ ችሏል። ሐብታሙ ግቡን ባስቆጠረበት ወቅት ከሮበርት ኦዶንካራ ጋር በመጋጨቱ ጉዳት አስተናግዶ ለተወሰኑ ደቂቃዎች የህክምና እርዳታ ተደርጎለት ወደ ወደ ሜዳ ተመልሷል።

ሲዳማ ቡናዎች ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ትኩረታቸውን መሪነታቸውን በማስጠቅ ላይ አድርገው ተንቀሳቅሰዋል። አዳማ ከተማዎችም የተደራጀውን የሲዳማ የተከላካይ መስመር ሰብረው ግብ ለማስቆጠር የተቸገሩ ሲሆን ጥቂት የግብ አጋጣሚዎችን ግን መፍጠር ችለዋል። 55ኛ ደቂቃ ላይ ከንዓን ማርክነህ እና በረከት ደስታ አንድ ሁለት ተጫውተው ይዘው የገቡትን ኳስ ከነዓን ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረው፣ 72ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ከበረከት ደስታ ከቀኝ መስመር የተሻማለትን ኳስ ከነዓን ሳይጠቀምበት የቀረው እንዲሁም 88ኛው ደቂቃ ላይ ከቅኝ ጠርዝ የተገኘውን የቅጣት ምት ኢስማኤል ሳንጋሪ ቀጥታ ወደግብ መትቶ ግብ ጠባቂው በአስደናቂ ሁኔታ ያዳነበት የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር።

ሲዳማዎች ከጎሉ በኋላ ሰንዴይ ሙቱኩን ቀይረው በማስገባት በመከላከል ቀጠናው የተጫዋች ቁጥር ከማብዛታቸው በተጨማሪ የከነዓን ማርክነህን እንቅስቃሴ በመከታተል እንዲገታ ሚና በመስጠት የተጫወቱ ሲሆን 65ኛው ደቂቃ ላይ ሐብታሙ ገዛኸኝ ከመስመር ያቀበለውን ኳስ ወንድሜነህ ዓይናለም ወደግብ አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው ካዳነበት ሙከራ ውጪ የጠራ የግብ አጋጣሚ መፍጠር ባይችሉም የጨዋታዋን ብቸኛ ጎል አስጠብቀው 1-0 አሸንፈው ወጥተዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ሲዳማ ቡና በ34 ነጥቦች 2ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ በአንፃሩ አዳማ ከተማ በ26 ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል ።



© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡