ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ወላይታ ድቻ ከ መከላከያ

የወላይታ ድቻ እና መከላከያን ጨዋታ እንደሚከተለው እናስዳስሳችኋለን።

መከላከያ በወራጅ ቀጠና ውስጥ ሆኖ በስድስት ነጥብ የሚበልጠው ወላይታ ድቻን ነገ በሶዶ ስታድየም ይገጥማል። በሁለተኛው ዙር መነቃቃትን ካሳዩ ቡድኖች መካከል የሚጠቀሰው ወላይታ ድቻ ከአንድ ሽንፈት ውጪ በሰበሰባቸው ነጥቦች ወደ ሰንጠረዡ ወገብ ለመድረስ እየጣረ ይገኛል። የነገውን ጨዋታ በድል ከተወጣም ከአደጋው ከመራቅ ባለፈ አንድ ደረጃ የማሻሻል ዕድል ይኖረዋል። ሦስተኛውን እና የከፋውን ሽንፈት በፋሲል የቀመሰው መከላከያ አሁንም አካሄዱን ማስተካከል አልቻለም። ለስምንት ጨዋታዎች ያለድል መጓዙን ተከትሎም ወራጅ ቀጠና ውስጥ ለመቀመጥ ተገዷል። የነገውን ጨምሮ ቀጣይ ጨዋታዎች ላይ የሚያገኛቸው ነጥቦችም ከበላዩ ያለው ደቡብ ፖሊስን ቦታ ለመረከብ እጅግ ወሳኝ ይሆናሉ።

በፈቡብ ፖሊሱ ጨዋታ ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ በገለልተኛ ሜዳ ለመጫወት የተገደዱት ወላይታ ድቻዎች ኳስን ተቆጣጥረው ለመጫወት ይሞክሩ እንጂ መሀል ላይ የበላይነት ሲወሰድባቸው ወደ መልሶ ማጥቃት አጨዋወት ለመዞር ሲዳዳቸው ይታያል። ከአቀራረብ አንፃር መከላከያ የኳስ ቁጥጥሩን ለመያዝ መሞከሩ አይቀሬ መሆንም ድቻዎችን በፈጣን ሽግግር ወደ ግብ አፋፍ መድረስን ምርጫቸው እንዲሆን ሊያደርግ ይችላል። ሆኖም ቡድኑ በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ የሚሰራቸው የቅብብል እና የውሳኔ ስህተቶች ዋጋ ሊያስከፍሉት ይችላሉ። የጦሩ የኋላ ክፍል ከጀርባው ክፍተት በሚተውባቸው ቅፅበቶች ግን በተለይም በቸርነት ጉግሳ በሚመራው የቡድኑ የግራ ወገን የጤና ንቦቹ አብዝተው ጫና ሊፈጥሩ ይችላሉ።

ዘርፈ ብዙ ችግሮች ያሉበት መከላከያ ከሁሉም ነገሮች በላይ በአዕምሮ እና በአካላዊ ዝግጁነት ላይ አተኩሮ ወደ ሜዳ መግባት ይጠበቅበታል። አሁንም ወሳኝ አጥቂው ምንይሉ ወንድሙን በጉዳት አበበ ጥላሁንን ደግሞ በቅጣት ሳቢያ የማይጠቀመው ጦሩ በቀላል ስህተቶች ግብ የሚያስተናግድበትን አኳኋንም ሙሉ ለሙሉ መቅረፍ ከጨዋታው ተፈላጊውን ውጤት ለማግኘት በእጅጉ ያስፈልገዋል። በተለይም እጅግ በፍጥነት ዝግ ያለው የመከላከል ሽግግሩ ከኋላ ያለውን ችግር እያባባሰበት ሲገኝ የመከላከል አደረጃጀቱ በቀላሉ መበታተን ለተጋጣሚው መልሶ ማጥቃት ተጋላጭ ሊያደርገው ይችላል። በመሆኑም ግብ ላለማስተናገድ መጠንቀቅ ያለበት እና ከአማካይ ክፍሉ በሚያገኛቸው ጥቂት ዕድሎች ግብ ማስቆጠር የሚጠበቅበት መከላከያ በነገው የሶዶ ጨዋታ በእጅጉ መፈተኑ የማይቀር ነው።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– እርስ በእርስ በተገናኙባቸው 11 የሊግ ጨዋታዎች ወላይታ ድቻ 12 ግቦችን አስቆጥሮ 5 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ነው። ከ4 አቻ ውጤቶች መመዝገብ ውጪም መከላከያ ሁለት ጊዜ ብቻ ድል ሲቀናው 6 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።

– ሶዶ ላይ ሽንፈት ያላገኘው ወላይታ ድቻ ዘንድሮ በሜዳው ካደረጋቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች አምስቱን በድል አራቱን ደግሞ በአቻ ውጤቶች አጠናቋል። በአጠቃላይ ውድድሩም ድሎች የቀኑት በሜዳው ላይ ጨዋታዎቹ ብቻ ነው።

– ከሜዳው ውጪ ዘጠኝ ጨዋታዎችን ያከናወነው መከላከያ ሁለቱን ብቻ በድል ሲወጣ በሦስቱ ነጥብ ተጋርቶ አራት ሽንፈቶች ገጥመውታል።

ዳኛ

– ዘንድሮ በዋና ዳኝነት ከተመደበባቸው ጨዋታዎች ውስጥ ሁለቱ ቡድኖች ከ ሀዋሳ ከተማ ጋር የተገናኙባቸውን ጨዋታዎች የዳኘው ቢኒያም ወርቅአገኘሁ ለዚህም ጨዋታ ይመራዋል። አርቢትሩ በአምስት ጨዋታዎች 32 የማስጠንቀቂያ እና አንድ የቀይ ካርዶችን ሲመዝ ሁለት የፍፁም ቅጣት ምቶችን ሰጥቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወላይታ ድቻ (4-1-3-2)

ታሪክ ጌትነት

እሸቱ መና – ደጉ ደበበ – ዐወል አብደላ – አንተነህ ጉግሳ

በረከት ወልዴ

ፀጋዬ አበራ – አብዱልሰመድ ዓሊ – ቸርነት ጉግሳ

ባዬ ገዛኸኝ – አላዛር ፋሲካ

መከላከያ (4-2-3-1)

አቤል ማሞ

ሽመልስ ተገኝ – ምንተስኖት ከበደ – አዲሱ ተስፋዬ – ዓለምነህ ግርማ

በኃይሉ ግርማ – ቴዎድሮስ ታፈሰ

ሳሙኤል ታዬ – ዳዊት እስጢፋኖስ – ፍሬው ሰለሞን

ተመስገን ገብረኪዳን – ፍፁም ገብረማርያም


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡