ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ስሑል ሽረ ከ ሀዋሳ ከተማ

ነገ ከሚደረጉት ጨዋታዎች መካከል ስሑል ሽረ እና ሀዋሳ ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በነበረው ጨዋታ የስነምግባር ግድፈት አሳይተዋል በሚል ሁለት ጨዋታዎችን ከሜዳቸው ውጪ በዝግ እንዲጫወቱ በዲስፕሊን ኮሚቴ የተወሰነባቸው ስሑል ሽረዎች ይግባኝ በመጠየቃቸው በሜዳቸው የሚያደርጉትን ይህን ጨዋታ ማሸነፍ የሌሎች ውጤት አይተው ከወራጅ ቀጠና ስለሚያወጣቸው ማሸነፍ ብቸኛ ምርጫቸው ነው። ባለፉት ጨዋታዎች ከሌላው የቡድን ክፍል በተሻለ ውጤታማ የሆነ የማጥቃት ጥምረት ያላቸው ስሑል ሽረዎች በዚህ ጨዋታም በዛ ውጤታማ ጥምረት መሰረት አድርገው ይጫወታሉ ተብሎ ሲጠበቅ በጉዳት ምክንያት የመሰለፉ ነገር ያለየለት ደሳለኝ ደባሽ የማይገባ ከሆነም አሳሪ አልመሃዲ ወደ ተፈጥራዊ ቦታው በመመለሰ አዲስ የአማካይ ጥምረት ያሳያሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ ውጪ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ዘጠኝ ግቦች ያስተናገደው የተከላካይ ክፍላቸው ለሃዋሳ ከተማዎች ቀጥተኛ አጨዋወት ትኩረት ሰጥቶ መግባት ይጠበቅበታል። የደሳለኝ ጉዳይ እንሳለ ሆኖ ስሑል ሽረዎች በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም።

በሁለተኛው ዙር ባሳዩይ ወጥነት የሌለው ብቃት ምክንያት ቀስ በቀስ ከደረጃ ሰንጠረኙ መንሸራተት ያሳዩት ሃዋሳ ከተማዎች ከሜዳ ውጪ የማሸነፍ መጥፎ ክብረ ወሰን ለመቀየር ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። እንደ ተጋጠሚያቸው ሁሉ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች አዳማ ከተማን ከሜዳቸው ውጪ ካሸነፉበት ጨዋታቸው ውጪ ማሸነፍ ያልቻሉት ሀዋሳዎች ከደረጃው ወገብ ላለመውረድ የሚደርጉት ወሳኝ ጨዋታቸው ነው።

ባለፉት ጨዋታዎች 3-5-2 መርጠው በአብዛኛው ከመስመር ለሁለቱ ግዙፍ አጥቂዎች በሚሻገሩ ኳሶች እና ከታፈሰ ሰለሞን በሚነሱ ኳሶች ለማጥቃት የሚሞክሩት ሃዋሳዎች በአጨዋወታቸው ላይ ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ ባይጠበቅም የስሑል ሽረን የመስመር አጨዋወት ለመመከት የሁለቱ የመስመር ተመላላሾቻቸውን ( wing backs) የማጥቃት እንቅስቃሴ ይቀንሳሉ ተብሎ ይጠበቃል። በሌላኛው ወገን ደግሞ የተከላካይ ክፍሉ የሰመረ የስሑል ሽረን የማጥቃት ጥምረት የማቆም ኃላፊነት ተሸክሞ ወደ ሜዳ ይገባል። ሀዋሳ ከተማዎች ገብረ መስቀል ዱባለን በጉዳት ይዘው ያላመሩ ሲሆን ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን ከሦስት ጨዋታዎች ቅጣት በኃላ ወደ ጨዋታ የሚመለስ ተጫዋች ነው።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– የቡድኖቹ የመጀመሪያ የፕሪምየር ሊጉ ግንኙነት በሰባተኛው ሳምንት ሀዋሳ ላይ ሲደረግ ሀዋሳ ከተማ 6-1 በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

– ስሑል ሽረዎች በሜዳቸው በስምንት ጨዋታዎች ነጥብ ሲጋሩ አንድ ጊዜ ተሸንፈው ባህር ዳርን ባስተናገዱበት ጨዋታ ብቸኛ የሜዳ ላይ ድላቸውን ማግኘት ችለዋል።

– ሀዋሳ ከተማ ካደረጋቸው አስር የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች አምስት ጊዜ ተሸንፎ በሦስቱ ነጥብ መጋራት የቻለ ሲሆን ሁለት ጊዜ ደግሞ በድል ተመልሷል።

ዳኛ

– ጨዋታው ለኢንተርናሽናል ዳኛ በዓምላክ ተሰማ የሊጉ አምስተኛው ጨዋታ ሲሆን በእስካሁኖቹ አራት ጨዋታዎች ሰባት የማስጠንቀቂያ ካርዶችን እና አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ሲሰጥ አንድ ተጨዋች ደግሞ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ አሰናብቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ስሑል ሽረ (4-2-3-1)
ሀፍቶም ቢሰጠኝ

አብዱሰላም አማን – ዮናስ ግርማይ – ዲሜጥሮስ ወልደሥላሴ – ረመዳን የሱፍ

ሐብታሙ ሽዋለም – አሳሪ አልመሃዲ

ሳሊፉ ፎፋና – ያስር ሙገርዋ – ቢስማርክ አፓንግ

ቢስማርክ አፒያ

ሀዋሳ ከተማ (3-5-2)

ሶሆሆ ሜንሳህ

አዲስዓለም ተስፋዬ – መሣይ ጳውሎስ – ላውረንስ ላርቴ

ዳንኤል ደርቤ – ታፈሰ ሰለሞን – ሄኖክ ድልቢ– ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን – ደስታ ዮሀንስ

አዳነ ግርማ – እስራኤል እሸቱ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡