ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ፋሲል ከነማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

በፋሲል እና ድሬዳዋ ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

የዐፄ ፋሲለደስ ስታድየም ነገ 09፡00 ላይ ፋሲል ከነማ ከድሬዳዋ ከተማ የሚያደርጉትን ጨዋታ ያስተናግዳል። መከላከያ ላይ አራት ግቦችን በማዝነብ ሁለተኛ ደረጃን የተቆናጠጡት ዐፄዎቹ ከዚህ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ በማግኘት የመቐለ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታን በዓይነ ቁራኛ ይከታተላሉ። መሪዎቹ አዲስ አበባ ላይ ውጤት ካጡም ፋሲሎች ድል ከቀናቸው የነጥብ ልዩነቱን ወደ አምስት ዝቅ በማድረግ የዋንጫ ፉክክሩን ይበልጥ ነብስ ሊዘሩበት ይችላሉ። ሦስት ተከታታይ ድሎችን ያስኩት ድሬዳዋ ከተማዎች ከአደጋው ክልል በስምንት ነጥቦች የራቁ ሲሆን ነገም ለባለሜዳዎቹ ፈተና መሆናቸው የሚቀር አይመስልም። እስካሁን ሁለት ጊዜ ብቻ ሽንፈት ያስተናገዱት እና በሜዳቸው እጅ ያልሰጡትን ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈው ከተመለሱም ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ የሚያደርጉት ጉዞ የሚሳካ እና ከስጋትም ነፃ ወደ መሆኑ የሚቃረቡ ይሆናል።

በመከላከያው ጨዋታ ተከላካዮችን ከቦታቸው በማስነቀል በአጫጭር ቅብብሎቻቸው ክፍተቶችን እየፈስጥሩ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ያደርጉ የነበሩት ፋሲሎች የአጨራረስ ብቃታቸውም ከፍ ብሎ ታይቷል። በርግጥ ድሬዎችን በዛ መጠን ማጥቃት ቀላል ባይሆንም በጨዋታው ፋሲሎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ኖሯቸው የሜዳውን ስፋት በመጠቀም አጥቅተው እንደሚጫወቱ ይጠቀማል። የሱራፌል ዳኛቸው እና ኤፍሬን ዓለሙ የአማካይ ክፍል ጥምረትም ፍሬድ መሸንዲ እና ሚኪያስ ግርማን የተከላካይ ሽፋን ለማለፍ የሚያደርገው ጥረት ተጠባቂ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ዐፄዎቹ ሦስት የተከላካይ መስመር ተጫዋቾችን በመጠቅም ከወገብ በላይ ያለውን የቡድናቸውን ተሳላፊዎች ቁጥር በመጨመር ይበልጥ ጫና ሊፈጥሩም ይችላሉ። ይህን ለማድረግ በእጅጉ አስፈላጊ የሆነው ያሬድ ባየህ መመለስ ለአሰልጣኝ ወበቱ ትልቅ ዜና ሲሆን ሁኔታው ሙጂብ ቃሲምንም ወደ ፊት አጥቂነቱ የመመለስ ዕድሉ የሰፋ ነው።

ጉዳት ላይ የከረመው ፍቃዱ ደነቀ እና ቅጣት ተጥሎበት የጨረሰው በረከት ሳሙኤልን የያዘው ድሬዳዋ ከተማ በነገው ጨዋታ ራምኬል ሎክ ፣ ያሬድ ዘውድነህ እና ምንያህል ተሾመን በጉዳት ሳቢያ ያጣል። ጥንቃቄን በመምንጥ ከተከላካይ አማካዮቻቸው ባለፈ የማጥቃት ባህሪ ለተላበሱት ቀሪዎቹ አማካዮቻቸውም የፋሲልን የኳስ ፍሰት የማቋረጥ ኃላፊነት ሊሰጡ የሚችሉት ድሬዎች ለኢታሙና ኬይሙኒ በሚያደርሷቸው ኳሶች ጥቃት መሰንዘራቸው አይቀርም። ላይቤሪያዊው አጥቂ ከቅጣት መልስ ግብ ወደ ማስቆጠሩ መመለሱ ደግሞ ለአሰልጣኝ ስምዖን ዓባይ ቡድን ተጨማሪ ጉልበት ይሆናል። ነገር ግን ኢታሙና በፋሲል ጠንካራ የተከላካይ ክፍል እንዳይታፈን እንደ ረመዳን ናስር ያሉ የፈጠራ ብቃታቸው ከፍ ያሉ እና ጎል በማስቆጠሩም እየተሳካላቸው የመጡ አማካዮች በተለይም በማጥቃት ሽግግር ወቅት ለአጥቂው ቀርበው የመጫወት ኃላፊነት ሊሰጣቸው ይችላል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ቡድኖቹ በሊጉ አምስት ጊዜ ተገናኝተው አንድ አንድ ጊዜ የተሸናነፉ በሦስቱ አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ እኩል ሁለት ሁለት ግቦችንም አስቆጥረዋል።

– ፋሲል ከነማ ሜዳው ላይ ዘንድሮ ያለሽንፈት የዘለቀባቸውን አስር ጨዋታዎች አድርጎ ስድስት ድሎች እና አራት የአቻ ውጤቶች አስመዝግቧል።

– ከአስር የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ሁለቴ ድል የቀናቸው ድሬዳዋ ከተማዎች አምስት ጊዜ ደግሞ አንድ ነጥብ ይዘው ሲመለሱ ሦስቴ ሽንፈት ገጥሟቸዋል።

ዳኛ

– ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ የዓመቱ 12ኛ ጨዋታውን ይመራዋል። ፋሲልን ከሽረ ድሬዳዋን ደግሞ ከጊዮርጊስ ያጫወተው አርቢትሩ እስካሁን በዳኘባቸው 11 ጨዋታዎች 40 የማስጠንቀቂያ ካርዶችን ሲመዝ 2 የቀይ ካርድ እና 3 የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔዎችንም አሳልፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ፋሲል ከነማ (3-4-3)

ጀማል ጣሰው

ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን

ኤፍሬን ዓለሙ – ሐብታሙ ተከስተ – ሱራፌል ዳኛቸው – ሰለሞን ሐብቴ

ኢዙ አዙካ – ሙጂብ ቃሲም – ሽመክት ጉግሳ

ድሬዳዋ (4-2-3-1)

ሳምሶን አሰፋ

ገናናው ረጋሳ – አንተነህ ተስፋዬ – ዘነበ ከበደ – ሳሙኤል ዮሐንስ

ፍሬድ ሙሸንዲ – ሚኪያስ ግርማ

ኤርሚያስ ኃይሉ – ኤልያስ ማሞ – ረመዳን ናስር

ኢታሙና ኬይሙኒ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡