ሪፖርት | አዳማ ከተማ በዱላ ሙላቱ ብቸኛ ግብ ኢትዮጵያ ቡናን አሸንፏል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 22ኛ ሳምንት መርሀግብር በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም አዳማ ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን አስተናግዶ በዱላ ሙላቱ ብቸኛ ግብ 1-0 አሸንፏል።

አዳማ ከነማ በመቐለ 70 እንደርታ 2-1 ከተሸነፈው ስብስብ ተስፋዬ በቀለ፣ በረከት ደስታ፣ ሱራፌል ዳንኤል፣ ብሩክ ቃልቦሬ እና ሱለይማን ሰሚድን በማሳረፍ ሱለይማን መሀመድ ፣ ሙሉቀን ታሪኩ ፣ ከንዓን ማርክነህ ፣ ቴውድሮስ በቀለ እና መናፍ አወልን በመተካት ነበር ወደ ሜደ የገቡት። በእንግዳዎቹ በኢትዮጵያ ቡና በኩል አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ባህር ዳር ከተማን አስተናግደው 5 – 0 ካሸነፈው ስብስባቸው ቅጣት ላይ የሚገኘው አቡበከር ነስሩን በፍፁም ጥላሁን አልሀሰን ካሉሻን በአማኑኤል ዮሀንስ ተክተው ነበር ወደ ሜደ የገቡት።

ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ባለፈዉ ሳምንት አጋማሽ ላይ ባልታወቁ ሰዎች ተኩስ ተከፍቶ ጥቃት ተፈፅሞባቸው ህይወቱን ላጣው የዋልታ ፖሊስ ተጫዋች አማኑኤል ብርሃኔ የህሊና ፀሎት ተደርጓል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበተ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ማሀል ሜዳ ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ ታይቷል። በሙከራ ደረጃ እንግዳዎቹ ገና በጨዋታው መጀመሪያ ላይ ከሁሴን ሻባኒ የተሻጋረለትን ኳስ አማኑኤል ዮሃንስ ከሳጥን ጠርዝ ወደ ግብ አክርሮ ሞክሮ ግብ ጠባቂ ያዳነበት የሚጠቀስ ነበር። በቀጣይ 15 ደቂቃዎች የተሻለ ተጭነው የተጫወቱት ባለሜዳዎቹ ወደ ቀኝ መስመር ባመዘነው የማጥቃት እንቅስቃሴ በቡልቻ ሹራ እና በኤፍሬም ዘካርያስ በተከታታይ ደቂቃዎች ኳስ ወደሳጥን ይዘው በመግባት ወደግብ ሙከራ ቢያደርጉም በኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች የተመለሰባቸው አጋጣሚዎች ጥሩ የሚባሉ የማጥቃት ሂደት ነበሩ።

በጨዋታው ላይ ድንቅ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የተስተዋለው ቡልቻ ሹራ 26ኛ ደቂቃ ላይ ለሱሌማን መሀመድ ከግራ መስመር ወደ ሳጥን ውስጥ ያሻገረለትን ኳስ ሱሌማን ወደግብ በቀጥታ ቢመታም ኢላማውን ያልጠበቀው ሌላ የሚጠቀስ አጋጣሚ ነው። በሌላ ሙከራ በመስመር መልሶ ማጥቃት ጠንካራ የነበሩት አዳማዎች 29ኛ ደቂቃ ላይ ከንዓን ማርክነህ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ከሳጥን ውጪ አዲስ ህንፃ ቀጥታ ወደግብ ሞክሮ ግብ ጠባቂ በጥሩ ሁኔታ መልሶበታል። ቦታ በመቀያየር የቡናን ተከላካዮች ሲፈትን የነበረው ከነዓን ማርክነህ 44ኛ ደቂቃ ላይም በግራ መስመር ሳጥን ውስጥ ይዞት የገባውን ኳስ ቀጥታ ወደግብ አክርሮ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርጓል። በ ድጋሜ 45ኛ ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት በቀኝ መስመር እየገፋ ይዞት የገባውን ኳስ ቡልቻ ሹራ በቀጥታ ወደግብ አክርሮ ሲመታ የግቡ የቀኝ ቋሚ የመለሰበት በመጀመሪያው አጋማሽ የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር ።

በኢትዮጵያ ቡና በኩል መሀል ሜዳ ላይ ያተኮረ እንቅሰቃሴ ቢያደርጉምየማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ የጎላ ተሳትፎ አልነበራቸውም። በሙከራ ደረጃ 24ው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ከርቀት ሁሴን ሻባኒ ወደግብ አክርሮ የመታውን ኳስ ሮበርት ኦዶንካራ በቀላሉ ያዳነበት የሚጠቀስ ሲሆን በድጋሜ 42ኛ ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጭ ሁሴን ሻባኒ ወደ ግብ አክርሮ የመታውን ኳስ ሮበርት ኦዶንካራ ወደ ውጭ ያወጣበት ጥሩ የሚባል መከራቸው ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ የቀዘቀዘ ጨዋታ ቢያደርጉም ከሁለቱ ቡድኖች የተሻለ ለማጥቃት ቅርብ የነበሩት ባለሜዳዎቹ ነበሩ። 53ኛው ደቂቃ ላይ ከንዓን ማርክነህ ሳጥን ውስጥ ይዞት የገባውን ኳስ ከግብጠባቂ ጋር ተገናኝቶ  ወደግብ በሚመታበት ሰዓት አህመድ ረሽድ ደርሶ ያዳነበት የሚጠቀስ ኳስ ነበር። አዳማዎች ወደ መስመር ባዘነበለው የማጥቃት እንቅስቃሴ በከንዓን ማርክነህ ፣ሱሌማን መሀመድ እና ቡልቻ ሹራ በግራ መስመር በጣም ተጭነው በመጫወት የኢትዮጵያ ቡናን የተከላካይ ክፍል ሲፈትኑት ይስተዋል ነበር። በዚህም ብቸኛዋን ግብ ሲያስቆጥሩ በግራ መስመር 73ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት የተገኘውን ኳስ ቡልቻ ሹራ ይዞት በመግባት ወደ ቀኝ መስመር ተቀይሮ ለገባው ዱላ ሙላቱ አሻግሮለት ዱላ ወደግብ በመቀየር አዳማ ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል።

አዳማ ከነማዎች ግብ ካስቆጠሩ በኋላ የተሻለ የመከላከል ክፍላቸውን በማጠናከር ወጤት ለማስጠበቅ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ አዲስ ህንፃ ከቡልቻ ሾራ የተሻገረለትን ኳስ በቀጥታ ወደግብ የመታው ኳስ ድንቅ የሚባል መከራ ነበር። በድጋሚ  ከግብ ጠበቂው የተመለሰውን ኳስ ከሳጥን ውጭ ያገኝው ኢስማኤል ሳንጋሪ በቀጥታ አክርሮ የመታው ኳስ ወንደሰን አሸናፊ ሊያድንበትም ችሏል።

ኢትዮጵያ ቡናዎች የተወሰኑ የግብ ሙከራዎች ቢያደርጉም ነጥብ መጋራት የሚያስችላቸውን የግብ አጋጣሚ መፍጠር አልቻሉም። ከነዚህም ውስጥ 57ኛ ደቂቃ ላይ ከቀኝ ጠርዝ ከዳንኤል ደምሱ የተሻገረለትን አስራት ቱንጅ በቀጥታ ወደ ግብ የመታውን ግብ ጠባቂ ያዳነበት የሚጠቀስ አጋጣሚ ነው። 88ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ክሪዚስቶም ንታምቢ ከርቀት የመታው ኳስ የሮበርት ኦዶንኮራን መዘናጋት ተከትሎ አስደናቂ ከመረብ ለማረፍ ተቅርቦ ነበር።

ጨዋታው በአዳማ 1-0 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ባለሜዳዎቹ 10ኛ ደረጃ ላይ በ29 ነጥብ ሲቀመጡ ኢትዮጵያ ቡና በአንፃሩ በ32 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡