ምስራቅ አፍሪካ | ኤርትራ የሴካፋ ከ15 ዓመት በታች ዋንጫ ልታዘጋጅ ነው

የኬንያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት እና የወቅቱ የሴካፋ ፕሬዝዳንት ኒክ ምዌንድዋ ኤርትራ ሴካፋ ከ15 ዓመት በታች ዋንጫ እንደምታዘጋጅ ተናገሩ።

ባለፈው ወር የሠላም እና ወዳጅነት ዋንጫን የማዘጋጀት ውጥኗ በአንዳንድ ጉዳዮች ያልተሳካላት ኤርትራ የመጀመርያው የሴካፋ ከ15 ዓመት በታች ዋንጫን እንደምታዘጋጅ ከወደ ኬንያ ተሰምቷል። የኬንያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከግብፁ ክለብ ዋዲ ዴግላ ጋር አብሮ ለመስራት በተስማማበት መድረክ ላይ ተገኝተው ሃሳበቸው የገለፁት የወቅቱ የሴካፋ ፕሬዝደንት ኒክ ምዌንድዋ የቀጠናው የወጣቶች የእግር ኳስ ለማሳደግ በቀጣዩ ኦገስት (ነሀሴ) የመጀመርያው ከአስራ አምስት ዓመት በታች የሴካፋ ዋንጫ በኤርትራ ለማዘጋጀት እንደወሰኑ ገልፀዋል። ፕሬዝዳንቱ ውድድሩ መዘጋጀቱ ለቀጠናው እግር ኳስ እድገት ወሳኝ እንደሆነ አውስተዋል። ” ይህ ውድድር ለማዘጋጀት ያሰብነው በቀጠናው ለታዳጊዎች እግር ኳስ የሚሰጠውን ትኩረት ከፍ ለማድረግ ነው።” ብለዋል።

በአሰልጣኝ ዓለምሰገድ ኤፍሬም እየተመሩ ከሃያ ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸው ተጫዋቾች ይዘው ላለፉት አራት ወራት የሠላም ዋንጫን በመጠባበቅ የነበሩት “የቀይ ባህር ግመሎች” በቀጣይ ቀናት የተጫዋቾች ምርጫ በማድረግ ዝግጅት ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡