ቅዱስ ጊዮርጊስ የሦስት ተጫዋቾችን ግልጋሎት በዚህ ዓመት አያገኝም

ያለፉትን ወራት በተለያዩ ጉዳቶች ምክንያት ከሜዳ የራቁት ሳላዲን ሰዒድ፣ ጌታነህ ከበደ እና መሐሪ መና በዘንድሮ የውድድር ዘመን ወደ ሜዳ ተመልሰው ፈረሰኞቹን እንደማያገለግሉ ተረጋገጠ።

ሳላዲን ሰዒድ ባሳለፍነው ወር ካደረገው የትርፍ አንጀት ቀዶ ጥገና በኋላ ከህመሙ በማገገሙ ያለፉትን አስራ አምስት ቀናት ልምምዶች እየሰራ በመቆየቱ ባሳለፍነው እሁድ በተካሄደው የሸገር ደርቢ ጨዋታ ላይ ይሰለፋል ተብሎ ቢጠበቅም የትርፍ አንጀት ህመሙ በድጋሚ በመነሳቱ ዳግመኛ ቀዶ ጥገና ለማድረግ ተገዷል።

በዓመቱ መጀመርያ የኢትዮጵያ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ከመከላከያ ጋር በነበረው ጨዋታ ወደ መጨረሻው ደቂቃ የጉልበት ጉዳት አስተናግዶ ተቀይሮ ከወጣ በኋላ ያለፉትን ስምንት ወራት ወደ ሜዳ ያልተመለሰው የግራ መስመር ተከለካዩ መሐሪ መና ወደ ህንድ በማቅናት የተሳካ ቀዶ ጥገና አድርጎ መመለሱ ታውቋል። መሐሪ በአሁን ሰዓት የህክምና ባለሙያዎቹ በሰጡት ትዕዛዝ መሠረት ከአንድ ወር በኋላ የጂም ላይ ልምምድ የሚጀምር ሲሆን ከሦስት በኃላ ደግሞ ወደ ሜዳ በመመለስ ልምምድ መስራት እንደሚጀምር ሰምተናል ።

እንዲሁ የጉልበት ጉዳት በማስተናገዱ ምክንያት ለወራት ከሜዳ የራቀው አጥቂው ጌታነህ ከበደ ወደ ህንድ አቅንቶ የተሳካ የተባለ ህክምናውን አጠናቆ የተመለሰ ቢሆንም ከነሐሴ ወር በፊት ወደ ሜዳ ላይመለስ እንደማይችል ታውቋል።

በተያያዘ የቅዱስ ጊዮርጊስ ዜና በጉዳት ያለፉትን ሳምንታት ከሜዳ የራቀው ምንተስኖት አዳነ አገግሞ ልምምድ መጀመሩን ለማወቅ ችለናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡