ሁለት የፕሪምየር ሊጉ ተጫዋቾች የየሀገራቸው የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመርያ ስብስብ ውስጥ ተካተዋል

የቅዱስ ጊዮርጊሱ ኬንያዊ ግብጠባቂ ፓትሪክ ማታሲ እና የኢትዮጵያ ቡናው ቡሩንዲያዊ አጥቂ ሑሴን ሻባኒ በአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ በየሀገራቸው የመጀመርያ የተጫዋቾች ዝርዝር ውስጥ ተካተቱ።

ከ2017 አንስቶ የሃገሩ ማልያ ለብሶ መጫወት የቻለው የ31 ዓመቱ ግብ ጠባቂ ፓትሪክ ማታሲ ከዚህ በፊት ሃገሩን በሴካፋ ጨምሮ በተለያዩ ማጣርያዎች ወክሎ የተጫወተ ሲሆን በማጣርያው ላይ በመጀመርያ ተመራጭነት እንደመጫወቱ ከሌሎች በዝርዝሩ ከተካተቱ ሦስት ግብጠባቂዎች ልቆ በአሰልጣኙ ምርጫ ወደ ግብፁ የአፍሪካ ዋንጫ የማምራት እድሉ ሰፊ ነው።

ሌላው ሃገሩን ለመወከል የተቃረበው ተጫዋች የኢትዮጵያ ቡና ቡሩንዲያዊው አጥቂ ሑሴን ሻባኒ ሲሆን እሱም እንደ ማታሲ በተመሳሳይ በመጀመርያውና 28 ተጫዋቾችን በያዘው ምርጫ ላይ ነው የተካተተው። በ2013 ሃገሩን መወከል የጀመረው የ28 ዓመቱ የቀድሞ የባሮካ እና የራዮን ስፖርትስ አጥቂ ለሃገሩ 13 ጨዋታዎች አድርጎ አንድ ጎልም ማስቆጠር ችሏል፤ ግቧም በአቋም መለኪያ ጨዋታ ሃገሩ ኢትዮጵያን ሃዋሳ ስቴድየም ላይ ስትገጥም ያስቆጠራት ነበረች። በሁለተኛው ዙር ኢትዮጵያ ቡናን ተቀላቅሎ ከቡድኑ ጋር ድንቅ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው ይህ ብሩንዳዊ አጥቂ ካለው ወቅታዊ ብቃት አንፃር በአሰልጣኝ ንዩንጌኮ የመጨረሻ ምርጫ ይካተታል ተብሎ ይጠበቃል።

ሌሎች ሃገራቸው በአፍሪካ ዋንጫ ይወክላሉ ተብለው የሚጠበቁት ተጫዋቾች ዩጋንዳዊያኑ የአዳማ ከተማ ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ እና የኢትዮጵያ ቡና ተከላካይ ክሪዚስቶም ንታምቢ፣ የድሬዳዋ ከተማው ናሚቢያዊ አጥቂ ኢታሙኑዋ ኬሙይኔ ሲሆኑ የወልዋሎው ጊኒ ቢሳዊው ግብ ጠባቂ ዓብዱልዓዚዝ ኬይታም ባለው ወቅታዊ ብቃት ከረጅም ጊዜ በኋላ ሃገሩን የሚወክልበት ዕድል ሊኖር እንደሚችል ይገመታል።

አሁን ባለው መርሐ ግብር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚጠናቀቀው ሰኔ 16 ከመሆኑ አንፃር ሰኔ 14 ለሚጀምረው የአፍሪካ ዋንጫ የሚመረጡ ተጫዋቾች በመጨረሻዎቹ የሊግ ጨዋታዎች ክለባቸውን ላያገለግሉ ይችላሉ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡