ፕሪሚየር ሊግ – ኤሌክትሪክ ደረጃውን ያሻሻለበትን ድል አስመዝግቧል

አወዛጋቢ የዳኝነት ውሳኔዎች ተበራክተዋል

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 6ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድየም ተካሂዶ ኤሌክትሪክ አርባምንጭን አሸንፏል፡፡

ቀዝቀዝ ባለ እንቅስቃሴ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመርያ አጋማሽ 0-0 ተጠናቋል፡፡ ከእረፍት መልስ ተቀይሮ የገባው ብሩክ አየለ በ77ኛው ደቂቃ ከማእዘን የተሻገረችውን ኳስ በግንባሩ በመግጨት የኤሌክትሪክን ቀዳሚ ግብ ሲያስቆጥር ናይጄርያዊው ፒተር ኑዋድኬ በ83ኛው ደቂቃ የኤሌክትሪክን 2ኛ ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡

ሊጉ ዛሬም አጨቃጫቂ የዳኝነት ውሳኔ አላጣውም፡፡ ግብ አስቆጣሪው ፒተር በ90ኛው ደቂቃ በአርባምንጭ የግብ ክልል ሳይነካ ወድቋል በሚል የእለቱ ዳኛ በአጨቃጫቂ ሁኔታ በ2ኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ አሰናብተውታል፡፡ ተጫዋቹ የዳኛውን ውሳኔ የተቃወመ ሲሆን ኤሌክትሪክ ክስ ሲያሲዝም ተስተውሏል፡፡

ኤሌክትሪክ ድሉን ተከትሎ ከወራጅ ቀጠናው በመውጣት 9ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል፡፡ በአንጻሩ አርባምንጭ ከነማ በ4 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ተገዷል፡፡

የሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ አዳማ ከነማ በ16 ነጥቦች ሲመራ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ13 ነጥብ ይከተላል፡፡ የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን ደግሞ የደደቢቱ ሳሚ ሳኑሚ በ5 ግቦች ይመራል፡፡

የ7ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሀሙስ ሲደረጉ ጎንደር ላይ ዳሽን ቢራ ኤሌክትሪክን ፣ ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከነማ አዳማ ከነማን ፣ ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከነማ ንግድ ባንክን ፣ አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከነማ ኢትዮጵያ ቡናን ፣ ይርጋለም ላይ ሲዳማ ቡና መከላከያን ፣ ሆሳእና ላይ ሀዲያ ሆሳእና ወላይታ ድቻን በተመሳሳ 9፡00 ላይ ያስተናግዳሉ፡፡ በ11፡30 ደደቢት ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአዲስ አበባ ስታድየም ይጫወታሉ፡፡

ከ7ኛው ሳምንት ጨዋታዎች በኋላ ፕሪሚየር ሊጉ በቻን ውድድር ምክንያት ለቀጣዮቹ 45 ቀናት ተቋርጦ በየካቲት ወር ላይ ይጀምራል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *