ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | የ27ኛ ሳምንት የዕሁድ ጨዋታዎች

ዛሬ በድሬዳዋ እና መቐለ የሚከናወኑትን ሁለት ጨዋታዎች በዳሰሳችን በአንድነት ተመልክተናቸዋል።

ድሬዳዋ ከተማ ከ ስሑል ሽረ

ከወራጅ ቀጠናው ከፍ ብሎ የተቀመጠው ድሬዳዋ እና  ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው ሽረን በሚያገናኘው ይህ ጨዋታ ሁለቱም በተመሳሳይ የቅርብ ተፎካካሪዎቻቸውን ውጤት አይተው ወደ ጨዋታው በመምጣታቸው በተመሳሳይ ማሸነፍን ያልማሉ።

ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ጥሩ ውጤት አምጥተው ከወራጅ ቀጠናው መራቅ ያቻሉት ብርቱካናማዎቹ ባለፉት የሜዳ ውጪ ጨዋታዎቻቸው ድል ማስመዝገብ ቢሳናቸውም በሜዳቸው ያላቸው የማሸነፍ ክብረ ወሰን ግን በጥሩ ጎን የሚነሳ ነው። ባለፈው ከቅዱስ ግዮርጊስ ጋር በነበረው ጨዋታ ይህ ነው የሚባል ጥሩ የማጥቃት አጨዋወት ያልነበራቸው ድሬዎች ከሁለተኛው ዙር መጀመር አንስቶ ጥሩ የፈጠራ አቅም ያዳበረው የአማካይ ክፍላቸው ለማጥቃት ጥረት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ድሬዎች በኩል በነገው ጨዋታ ረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የነበረው ራምኬል ሎክ እና ባለፈው ሳምንት ጉዳት የገጠመው ሳሙኤል ዮሃንስ እንዲሁም ከጉዳት ባይመለስም የብሔራዊ ቡድን ጥሪ የደረሰው ኢታሙና ኬይሙኒን ግልጋሎት አያገኙም።

ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያሳዩ ከሚገኙት ቡድኖች መሀል የሚጠቀሱት ስሑል ሽረዎች ይህ ጨዋታ ከተጋጣሚያቸው በላይ ለነሱ ወሳኝ ስለሆነ በልዩ ትኩረት እንደሚያከናውኑት ይገመታል። ባለፉት ጨዋታዎች በርካታ ተጫዋቾች በጉዳት አጥተው የነበሩት ሽረዎች ከግብ ጠባቂው ዳዊት አሰፋ ውጪ የሰንደይ ሮትሚ እና ዮናስ ግርማይን ከጉዳት መመለስ ጨምሮ ሙሉ ቡድኑ መልካም ጤንነት መገኝቱ የአሰልጣኙን ምርጫ ከመቼውም ግዜ በላይ ያሰፋል ተብሎ ይታሰባል። የውጤታማ መስመር አጨዋወት ባለቤት የሆኑት ሽረዎች ይህን አቀራረብ ይቀይራሉ ተብሎ ባይጠበቅም የላቀ የፈጠራ አቅም ያለውን የድሬ መሃል ክፍል በአግባቡ ለመመከት መሃል ሜዳ ላይ የቅርፅ ለውጥ ሊያደርጉ ይችላሉ።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ድሬዳዋ እና ሽረ ለመጀመሪያ ጊዜ በፕሪምየር ሊጉ የተገናኙበት የ12ኛ ሳምንት ጨዋታ 0-0 በሆነ ውጤት የተጠናቀቀ ነበር።

– ድሬዳዋ ከተማ ከተማ ሜዳው ላይ 13 ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን ሰባት የድል ፣  አራት የሽንፈት እና ሁለት የአቻ ውጤቶችን አስመዝግቧል። ድሬዎች ለመጨረሻ ጊዜ ካስተናገዷቸውን አራት ክለቦች ሁለቱን በ በ2-0 ሁለቱን ደግሞ በ2-1 ውጤት በመርታት ሙሉ ነጥብ መስብሰብ ችለዋል። 

– ስሑል ሽረ ከሜዳው ውጪ 12 ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን በስምንቱ የሽንፈት ፣ በሦስቱ የአቻ እንዲሁም በአንዱ የድል ውጤቶችን አስመዝግቧል።                                                                          

ዳኛ

– ጨዋታው ዘንድሮ ለኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ አስረኛ ጨዋታው ይሆናል። አርቢትሩ በእስካሁኖቹ ስምንት ጨዋታዎች 31 የማስተጠንቀቂያ ካርዶች እና አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔዎችን አሳልፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ 

ስሑል ሽረ ( 4-2-3-1)

ሰንደይ ሮቲሚ

ዓብዱሰላም አማን – ብሩክ ተሾመ – አሳሪ አልመሃዲ – ረመዳን የሱፍ

ሀብታሙ ሸዋለም – ደሳለኝ ደባሽ 

ቢስማርክ አፖንግ –  ያስር ሙገርዋ – ቢስማርክ አፒያ

ሳሊፉ ፎፋና

ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)

ሳምሶን አሰፋ

ገናናው ረጋሳ – አንተነህ ተስፋዬ – በረከት ሳሙኤል – ዘነበ ከበደ

 ፍሬድ ሙሸንዲ – ሚኪያስ ግርማ 

ኤርሚያስ ኃይሉ – ምንያህል ተሾመ – ረመዳን ናስር 

ሀብታሙ ወልዴ

ደደቢት ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ደደቢት ሊጉን መሰናበቱን ካረጋገጠ አንድ ሳምንት በኋላ ዛሬ ጊዮርጊስን ያስተናግዳል። ጨዋታው ሁለቱ ክለቦች ሲገናኙ ከዚህ ቀደም የነበረው ግርማ ሞገሱ ባይኖርም ፈረሰኞቹ ቢያንስ ትናንት ወደ ተሸነፈው ሲዳማ ቡና መጠጋት የሚችሉበትን ዕድል ሊሰጣቸው ይችላል። በአንፃሩ እንዳለ ከበደ ፣ ቢንያም ደበሳይ እና አለምአንተ ካሳን በጉዳት ለሚያጡት ደደቢቶች ግን ከመርሐ ግብር ማሟላት ያለፈ ትርጉም አይኖረውም። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በዚህ ዓመት ከማይመለሱት ከሳላዲን ሰዒድ ፣ ጌታነህ ከበደ እና መሀሪ መና ውጪ በጉዳት ዝርዝር ውስጥ የተካተተው ተጫዋች በኃይሉ አሰፋ ብቻ ነው።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን 19 ጊዜ ተገናኝተዋል።  ቅዱስ ጊዮርጊስ በ13 ጊዜ ድል ቅድሚያውን ሲወስድ ደደቢት ሶስት ጊዜ አሸንፎ ቀሪዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው። ቅዱስ ጊዮርጊስ 33 እንዲሁም ደደቢት 17 ጊዜ ኳስ እና መረብን ማገናኘት ችለዋል። 

– ደደቢት በቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ድል ያስመዘገበው ቡድኑ ዋንጫ ባነሳበት የ2005 የውድድር ዘመን 3-1 ባሸነፈበት ወቅት ነው።

– እስካሁን ከአዲስ አበባ ስታድየም ውጪ 11 ጨዋታዎችን ያደረገው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሦስቴ ድል የቀናው ሲሆን አራት ጊዜ በአቻ አራት ጊዜ ደግሞ በሽንፈት ተመልሷል።

– ደደቢት በትግራይ ስታድየም ላይ ባደረጋቸው 15 ጨዋታዎች ሁለት ድል እና አንድ የአቻ ውጤት ሲያስመዘግብ በሌሎቹ ተሸንፏል።

ዳኛ

– እስካሁን በዳኘባቸው አራት ጨዋታዎች 16 የመጀመሪያ እንዲሁም ሁለት ሁለተኛ የቢጫ እና አንድ የቀይ ካርዶችን የመዘዘው ዳንኤል ግርማይ ይህን ጨዋታ የመምራት ኃላፊነትን ወስዷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ደደቢት (4-2-3-1)

ረሺድ ማታውኪል

አብዱላዚዝ ዳውድ – ኃይሉ ገብረየሱስ – አንቶንዮ አቡዋላ – ሄኖክ መርሹ

ኤፍሬም ጌታቸው – አብርሀም ታምራት

መድሀኔ ብርሀኔ – የአብስራ ተስፋዬ – ፉሰይኒ ኑሁ

መድሃኔ ታደሰ      

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)

ፓትሪክ ማታሲ

ሄኖክ አዱኛ – አስቻለው ታመነ – ሳላዲን በርጌቾ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ

ናትናኤል ዘለቀ – ሙሉዓለም መስፍን – ታደለ መንገሻ

አቤል ያለው – ሪቻርድ አርተር – አሜ መሀመድ