አልሃሰን ካሉሻ ነገ ወደ ጋና ያመራል

ጉዳት የገጠመው አልሃሰን ካሉሻ ለህክምና ነገ ወደ ጋና ያመራል።

የዝውውር መስኮቱ ከመከፈቱ በፊት 70 እንደርታዎቹን ለመቀላቀል ተስማምቶ ላለፉት አምስት ቀናት ከቡድኑ ጋር ልምምድ ሲሰራ የቆየው ይህ ጋናዊ አማካይ በልምምድ ላይ ጉዳት የገጠመው ሲሆን የጉዳቱ መጠን እና ዓይነት አልታወቀም። ተጫዋቹ ወደ ጋና የሚያመራ ቢሆንም በመቐለ 70 እንደርታ የቻምፒየንስ ሊግ የተጫዋቾች ዝርዝር መካተቱን ለማወቅ ተችሏል።

በ2010 የውድድር ዓመት በኤሌክትሪክ መለያ የሊጉ ክስተት የነበረው ተጫዋቹ በተጠቀሰው ዓመት ምርጥ ብቃቱን አሳይቶ በሚቀጥለው ዓመት ወደ ኢትዮጵያ ቡና ቢዘዋወርም እንደተጠበቀው ሳይሆን ቀርቶ በዓመቱ መጨረሻ ከቡድኑ ጋር መለያየቱ ይታወሳል።

ከመቐለ ጋር በተያያዘ ዜና ጋናዊዎቹ ኦሴይ ማዊሊ እና ጋብሬል አህመድ ከእረፍት ተመልሰው የክለቡን ዝግጅት የተቀላቀሉ ሲሆን ሳሙኤል አቤኩ የተባለ ጋናዊ ተከላካይ ደግሞ ለሙከራ አምጥተዋል። ከዚ በፊት ለአሻንቲ ኮቶኮ፣ ኒው ኢዱቢያሴ እና ለሱዳኑ አልሂላል የተጫወተው አቤኩ በመሃል ተከላካይነት እና በመስመር ተከላካይነት መጫወት የሚችል ሲሆን በሦስት ጨዋታዎች ላይም የሃገሩ ጋና መለያን ለብሶ ተጫውቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡