ካፍ በዓምላክ ተሰማ ላይ ጥቃት በማድረስ የተከሰሱት ፋውዚ ሌካ ላይ ጥፋት አለማግኘቱን አስታወቀ

ካፍ ከሁለት ወራት በፊት የግብፁ ዛማሌክ የሞሮኮው አርኤስ በርካኔን አሸንፎ ዋንጫ ባነሳበት የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ፍፃሜ የመሐል ዳኛው በዓምላክ ተሰማ ላይ ጥቃት በመሰንዘር የተከሰሱት የሞሮኮ ሮያል እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ፋውዚ ሌካን ጥፋተኝነት የሚያረጋግጥ ማስረጃ አላገኘሁም ብሏል።

ካፍ ዛሬ ይፋ ባደረገው የዲሲፕሊን ቦርድ ውሳኔ ላይ እንደተጠቀሰው የጨዋታው ኮሚሽነር ጉስታቮ ንዶንግ ኤዱ አንዳንድ የአርኤስ በርካኔ ተጫዋቾች እና ኃላፊዎች የጨዋታው አመራሮች/ዳኞች ላይ ወከባ እንደፈፀሙ ከመገለፁ ውጪ ማን ላይ እንደተፈፀመ በግልፅ ያልተቀመጠ እና አሻሚነትን የሚፈጥር ነው። ስለዚህም የፋውዚ ሌካን ጥፋተኝነት የሚያረጋግጥ በቂ፣ ጠንካራ እና የተረጋገጠ መረጃ ማግኘት አልቻልኩም ብሏል።

በጉዳዩ ዙርያ ኢትዮጵያዊው ዳኛ በዓምላክ ተሰማ ከአፍሪካ ዋንጫ መልስ በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ለፋውዚ ሌካ ይቅርታ እንዳደረገለት መግለፁ ይታወሳል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡