ኢትዮጵያ ለ15 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሾመች

በኤርትራ አዘጋጅነት በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በሚካሄደው የሴካፋ ከ15 ዓመት በታች ውድድር ላይ የምትሳተፈው ኢትዮጵያ ዋና አሰልጣኝ ሾማለች።

አስራ አንድ የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች የሚሳተፉበት ከ15 ዓመት በታች ውድድር ከነሐሴ 9–26 (ውድድሩ የሚጀመርበት ቀን ሊቀየር ይችላል) በኤርትራ ይደረጋል። በምድብ ለ ከዩጋንዳ፣ ሩዋንዳ እና ደቡብ ሱዳን ጋር የተደለደለችው ኢትዮጵያ ከ15 ዓመት ቡድኗን በመያዝ በውድድሩ ላይ እንደምትሳተፍ ተረጋግጧል።

የቴክኒክ ኮሚቴው ትናንት ባደረገው ስብሰባ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ እና ረዳቶቹን መርጦ ሾማል። በዋና አሰልጣኝነት ያለፉትን ስድስት ዓመታት በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የሴቶች ቡድን እና ዘንድሮ ከ17 ዓመት በታች የወንድ ቡድን ዋና አሰልጣኝ በማሰልጠን በርካታ ታዳጊዎችን በማውጣት ስኬታማ ቆይታ እያደረገ የሚገኘው አሰልጣኝ ሰለሞን መካ ሲመረጥ የእርሱ ረዳት እንዲሆን ደግሞ የጥሩነሽ ዲባባ ወጣቶች አካዳሚ ከ20 ዓመት በታች አሰልጣኝ ሰለሞን ገለታ እንዲሆን ተመርጧል።

አሰልጣኝ ሰለሞን በቅርቡ ተጫዋቾችን በመምረጥ ዝግጅቱን የሚጀምር ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡