የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መግለጫ አዘጋጅቷል

የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌደሬሽን በእግር ኳስ ሊጎቻችን አደረጃጀት ላይ ያተኮረ የጥናት ውጤት ነገ ይፋ ያደርጋል፣ ከጥናቱ መቅረብ በኋላም ለሚዲያ መግለጫ ይሰጣል።

በኃይለየሱስ ፍስሃ (ኢ/ር) ፕሬዝዳንትነት የሚመራው የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌደሬሽን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የእግር ኳስ ሊጎችን አደራረጅት እና አካሄድ የሚመለከት ጥናት እያስጠና መሆኑን መግለፁ ይታወሳል። በዚህም መሰረት ባሳለፍነው ሳምንት ፌደሬሽኑ በቀጥተኛ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት (ክለቦች) ጋር ውይይት በማድረግ ለጥናቱ ተጨማሪ ግብዓት ሰብስቦ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል።

የዚህ የጥናት ውጤት ነገ 8 ሰዓት በጁፒተር ሆቴል ለሚመለከታቸው አካላት እንደሚቀርብ ታውቋል። ፌደሬሽኑ እንዳስታወቀው ከሆነ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን እና የስፖርት ኮሚሽን ተወካዮችን ጨምሮ በእግር ኳሱ አካባቢ ያሉ አካላት ነገ በቦታው ይገኛሉ። በሥነስርዓቱም ጥናቱ በአቶ ገዛኸኝ (የአዲስ አበባ ከተማ ክለብ ስራ አስኪያጅ) አማካኝነት ከቀረበ በኋላ ለብዙሃን መገናኛዎች መግለጫ እንደሚሰጥ ታውቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡