ቅዱስ ጊዮርጊስ ሦስተኛ ተጫዋች አስፈረመ

የተከላካይ መስመር ተጫዋቹ ደስታ ደሙ የፈረሰኞቹ ሦስተኛ ፈራሚ ሆነ።

ባለፈው የውድድር ዓመት ደደቢትን ለቆ ወልዋሎን በመቀላቀል ከቡድኑ ጋር ጥሩ ዓመት ያሳለፈው ይህ በመሃል ተከላካይነት እና በመስመር ተከላካይነት መጫወት የሚችለው ተስፈኛ ተከላካይ በዚህ የዝውውር መስኮት ከያብስራ ተስፋዬ እና አቤል እንዳለ በመቀጠል ፈረሰኞቹን የተቀላቀለው ሦስተኛ ተጫዋች ነው።

ለቻን ውድድር ማጣርያ ከጅቡቲ ጋር በነበረው የማጣርያ ጨዋታ ለዋናው ብሄራዊ ቡድን የመጀመርያው ጨዋታ ያደረገው ይህ ተከላካይ ባለፈው ዓመት በጉዳት ምክንያት ከፋሲል ጋር ካመለጠው ጨዋታ ውጭ ዓመቱን ሙሉ ቢጫ ለባሾቹን ማገልገል የቻለ ተጫዋች ሲሆን ቡድኑ ጥቂት ጎል ካስተናገዱ ክለቦች ተርታ እንዲሰለፍ ወሳኝ ሚና ተወጥቷል።

በሙገር ሲሚንቶ፣ ደደቢት እና ወልዋሎ መጫወት የቻለው ደስታ በቀጣይ ዓመት በቅዱስ ጊዮርጊስ ለቋሚ ተሰላፊነት ብርቱ ፉክክር ይጠብቀዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡