በሊግ አደረጃጀት ዙርያ ያተኮረ የጥናት ውጤት ይፋ ሆነ

በኢትዮጵያ እግር ኳስ የሚታየውን የሊግ ውድድር አደረጃጀት፣ አሰራር እና የሠው ኃይል ችግሮችን በተመለከተ የጥናት ውጤት ዛሬ በተሰጠ መግለጫ ይፋ ሆኗል።

በአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ፌደሬሽን አማካኝነት የተጠናው ይህ ጥናት ዛሬ ከሰዓት በጁፒር ኢንተርናሽናል ሆቴል ይፋ ሲሆን በስፍራው በርካታ የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል። የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ ኃይለሠማዕት መርሃጥብ (የአዲስ አበባ ከተማ የወጣቶች አደረጃጀትና የበጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ኃላፊ) ጨምሮ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ተወካዮች፣ የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚ አባላት፣ የተለያዩ የሙያ ማኅበራት ተወካዮች እና የሚዲያ አካላት ተገኝተዋል።

በመርሃ-ግብሩ መሰረት ጥናቱን ያሰጠናው የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ኃይለየሱስ ፍሰሃ (ኢ/ር) የመክፈቻ ንግግር አድርገው የእለቱን የክብር እንግዳ አቶ ኃይለሠማዕት መርሃጥበብን ወደ መድረኩ ጋብዘዋል። የክብር እንግዳውም የመግቢያ ንግግር በማድረግ ስነ-ስርዓቱን በይፋ አስከፍተዋል።

በመቀጠል አቶ ገዛኸኝ ወልዴ (የአዲስ አበባ ከተማ ክለብ ስራ አስኪያጅ) ጥናቱን አቅርበዋል። አቶ ገዛኸኝ በመጀመሪያ የተለያዩ የጥናት ዘዴዎችን ተጠቅመው ጥናቱን እንዳጠኑ ገልፀው በዋነኝነት የተጠቀሙትን የጥናት ዘዴ አስረድተዋል። በዚህም መሠረት በእግርኳስ ውድድር የተሰሩ ዓለማቀፍ ጥናቶችን እና የሃገር ውስጥ ሰነዶችን እንዳዩ አስረድተው ዘጠኝ የጥናቱን የዕይታ መስኮት (perspectives) መዘርዘር ጀምረዋል። በዚህም ከፍይናንስ አጠቃቀም አንፃር፣ ከመዋቅራዊ አስተዳደር አንፃር፣ ከእግርኳስ መርህ አንፃር፣ ከክልል ከተማ አስተዳደር እግርኳስ ፌደሬሽን ተሳትፎ አንፃር፣ ከፀጥታ ስፖርታዊ ጨዋነት፣ ከእግርኳስ ልማት አንፃር፣ ከስፖርት መሰረተ ልማት አንፃር፣ ጠንካራ ተከታታይነት ያለው ብሄራዊ ቡድን ከመገንባት አንፃር እና ከክለቦቻችን የአፍሪካ ውድድር ተሳትፎ አንፃር የሃገራችን ነባራዊ ሁኔታ በዝርዝር ገምግመዋል። አቶ ገዛኸኝ በግምገማቸው መሰረት የሃገራችን እግርኳስ አሁን ባለው አደረጃጀት እና አሰራር እንዳላደገ ገልፀው የተሻለ የሚሉትን ሁለት የምክረ ሃሳብ (መፍትሄ) አስቀምጠዋል።

የመጀመሪያው መፍትሄ “አሁን ያለውን የሊግ ውድድር አሰራር እና አደረጃጀት የሚተካ አማራጭ መቅረፅ” የሚል ነው። በዚህም መሰረት አሁን ያለው የሊግ ውድድር አሰራር በተቀመጡት መመዘኛዎች መሰረት አዋጭ አለመሆኑን በመግለፅ አማራጭ የሊግ አደረጃጀትና አሰራር እንዲቀረፅ አሰስበዋል።

በሁለተኝነት ደግሞ “የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ውድድርን ማድረግ” የሚል ነው። ግለሰቡ የተለያዩ ሃገራትን ተሞክሮ በማስረዳት ክልሎች ጠንካራ የውስጥ ውድድሮችን እንዲያደራጁ ማድረግ አለብን ብለዋል። ይህንን መፍትሄ ሲያስረዱ” የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው ክልሎች ጠንካራ የውስጥ ውድድሮችን እንዲያደራጁ በማድረግ እና ጠንካራ የእግርኳስ ፉክክር የሚታይበት የሊግ ውድድር በመፍጠር ከየክልሎቹ የተሻለ ውጤት የሚያስመዘግቡ ክለቦችን ደረጃውን በጠበቀ ከተማ እና ስታዲየም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አማካኝነት የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ውድድር ማድረግ የሚያስችል አደረጃጀት መፍጠር አለብን።” ብለዋል።

ጥናቱ ከቀረበ በኋላም በስፍራው ከተገኙ አካላት የተለያዩ ሃሳቦች ተነስተው ሃሳቦች ተንሸራሽረዋል። ከታዳሚያኑ ከተነሱት ነጥቦች መካከል ስለ አስተዳደራዊ ችግር፣ ስለ ስፖርታዊ ጨዋነት ችግር እና ስለ ቀጣይ እርምጃዎች ጥያቄ የተነሳ ሲሆን በጥናቱ ቢካተቱ የተባሉ ነጥቦችም ተነስተው ውይይት ተደርጓል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡