የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌደሬሽን መግለጫ ሰጠ

የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዛሬ ከሰዓት ያስጠናውን ጥናት ይፋ ካደረገ በኋላ ለሚዲያ አካላት መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ኃይለየሱስ ፍስሃ (ኢ/ር)፣ ምክትል ፕሬዝዳንት በለጠ ዘውዴ፣ ሦስት የፌደሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ አባላት እና ጥናቱን በበላይነት የመሩት አቶ ገዛኸኝ ወልዴ በጋራ ሰጥተዋል።

በመጀመሪያ የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት ኃይለየሱስ ፍስሃ ጥናቱን ሲያጠኑ ክለቦችን፣ ደጋፊ ማኅበራትን እና በስፖርቱ ያሉ አካላትን እንዳማከሉ በአጭሩ አስረድተዋል። “እኛ ጥናቱን ስናስጠና ክለቦችን ለማማከል ሞክረናል። በአዲስ አበባ ያሉ ክለቦችን ብቻ ሳይሆን በክልል ያሉ ክለቦችንም ጠይቀናል። በፕሪምየር ሊጉ ለሚሳተፉ ስድስት የክልል ክለቦች መጠይቅ ልከናል፤ ነገር ግን ሦስቱ ብቻ ነው ምላሽ የሰጡን። በከፍተኛ ሊግ ለሚወዳደሩ ስምንት ክለቦችም መጠይቅ ልከናል። ነገር ግን አምስቱ ምላሽ አልመለሱልንም። ይህ ብቻ ሳይሆን ለዳኞች፣ ኮሚሽነሮችን እና ለደጋፊ ማህበራትን መጠይቅ ልከናል።”ብለዋል።

በመቀጠል ከመግለጫው በፊት በቀረበው ጥናት ላይ ያተኮረ ጥያቄ ከብዙሃን መገናኛዎች ቀርቦ ምላሽ ተሰጥቷል።

ስለ ጥናቱ የአጠናን ሁኔታ (ገለልተኝነት)፣ ስለ ተቀመጡት መፍትሄዎች ትክክለኝነት፣ ጥናቱ ስላሳተፋቸው አካላት፣ ፌደሬሽኑ ከዋና የሃገሪቱ ፌደሬሽን ጋር ስላለው ግንኙነትና ሌሎች ጥናቱ ላይ ያተኮሩ ጥያቄዎች ተነስተዋል።

ስለ ጥናቱ አጠናን ምላሽ የሰጡት አቶ ገዛኸኝ” መታየት ያለበት ጥናቱ ስላገኛቸው ግኝቶች ነው። ጥናቱን ያጠናነው ዓለማቀፍ መመሪያዎችን ተከትለን ነው። ዋናው ሃሳባችን እግር ኳሳችን ወደተሻለ ነገር እንዲሄድ ነው። ስለዚህ ለምን በገለልተኛ አካል አልተጠናም የሚለውን ማየት የለብንም። ዋናው ጥናቱ የያዘው ነገር ነው።” ብለዋል። አቶ ገዛኸኝ ጨምረው ጥናቱን ሲያጠኑ እንደመነሻ ፕሪምየር ሊጉ በ1990 በአዲስ መልክ እንዲደረግ ሲወሰን የተጠና ጥናት ፈልገው እንዳጡና ከበፊቱ የሊግ ውድድር ጋር ማነፃፀር እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

ከአቶ ገዛኸኝ በመቀጠል የፌደሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ በለጠ ዘውዴ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል። “ከምንም በላይ መታየት ያለበት እኛ ጥናቱን ያስጠናንበትን ምክንያት ነው። በእኛ ስር ያሉ ክለቦች በተለያየ ጊዜ ጥያቄዎችን ስለሚያቀርቡልን ነው ጥናቱን ያጠናነው። ክለቦቻችን በተለያየ ጊዜ የሚያነሱትን ሃሳብ ለሚመለከተው አካል ለማቅረብ ደግሞ ጥናት ማጥናት አለብን። ስለዚህ ይህንን ተከትለን ነው የተጓዝነው። ማንኛውም ክለብ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ስር አልወዳደርም ብሎ ወደእኛ ከመጣ በህግ እና ደምባችን መሰረት እናወዳድራለን።” በማለት ጥናቱን ስላስጠኑበት አላማ አስረድተዋል።

አቶ በለጠ ጨምረውም ፌደሬሽናቸው ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ጋር ስላለው ግንኙነት ሃሳብ ሰጥተዋል።” በሁለታችን መካከል ምንም አዲስ ነገር የለም። ሁለታችንም ጥሩ ግንኙነት ነው ያለን። ጥናቱን ያስጠናነው እንደ ማንኛውም ስፖርት ውስጥ ያለ አካል ነው። ዛሬም ለፌደሬሽኑ ጥሪ አቅርበን ነበረ ነገር ግን ከፌደሬሽኑ በኩል አንድ ሰው ብቻ ነው የመጣው። ይህም የሆነው በተለያዩ ከአቅም በላይ በሆኑ ጉዳዮች እንደሆነ ነግረውናል። ስለዚህ በሁለታችን መካከል ምንም ነገር የለም።” ብለዋል።

በመቀጠል የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት አቶ ነጋሴ የተለየ ሃሳብ አንፀባርቀዋል። “እኔ በግሌ በጥናቱ አልተስማማሁም። እንደ ስፖርት ባለሙያ ከመጀመሪያ ጀምሮ ልዩነቴን ተናግሬያለሁ። በግሌ የራሴ መረጃ ስላለኝ ጥናቱን ተቃውሜያለው።” በማለት ከሌሎቹ የሥራ አስፈፃሚ አባላት የተለየ ሃሳብ እንዳላቸው ገልፀው በግላቸው በሚዲያ ሃሳባቸውን እንደሚያስረዱ ተናግረዋል።

መግለጫውም ተጨማሪ መብራራት አለባቸው በተባሉ ሃሳቦች ላይ ተጨማሪ ማብራሪያዎች ተሰጥተው ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡