ወላይታ ድቻ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ የማጠቃለያ ውድድር አሸናፊ ሆነ

ከነሐሴ 5–13 በስድስት ቡድኖች መካከል በፌዴሬሽኑ በኩል ትኩረት ተነፍጎት ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ዛሬ በተካሄዱ የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች ፍፃሜውን ሲያገኝ ወላይታ ድቻ የውድድሩ አሸናፊ ሆኗል።

04:00 አዳማ ከተማን ከአፍሮ ፅዮን ያገናኘው ጨዋታ በአዳማ ከተማ 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት አሸናፊነት ተጠናቋል። ብዙም ትኩረት የማይስብ እና ጎሎች ለማስቆጠርም ሆነ ያገኙትን የጎል አጋጣሚዎች ለመጠቀም ብዙም ፍላጎት ያልታየበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የአፍሮ ፅዮን ተከላካዮች በራሳቸው የሜዳ ክፍል የሚሰሩትን ተደጋጋሚ ስህተት ተጠቅመው አዳማዎች ጎል ማስቆጠር የሚችሉበትን ዕድል አጥቂው አቤል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። አምበል በመሆን ቡድኑን እየመራ እና የቡድኑን እንቅስቃሴ በማደራጀት በውድድሩ ላይ በግሉ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የተመለከትነው የአፍሮ ፅዮን አጥቂ እንድርያስ ለገሠ ካደረገው አንድ የጎል ሙከራ በቀር በአፍሮ ፅዮን በኩል ተጨማሪ ሙከራዎችን መመልከት አልቻልንም።

ከዕረፍት መልስ በጨዋታው ብቸኛው ጎል ከአሰልቺ የጨዋታ እንቅስቃሴ በኃላ 78ኛው ደቂቃ ተመዝግቧል። ከተሻጋሪ ኳስ በተከላካዮች ተደርቦ በአፍሮ ፅዮን የግብ ክልል የቀረውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ዮናስ አብነት ባስቆጠራት ጎል አዳማ ከተማ አሸናፊ ሆኗል። ውጤቱን ተከትሎም አዳማ ከተማ ከ20 ዓመት በታች የዙር ውድድር ካስመዘገበው እንቅስቃሴ አንፃር እጅጉን ወርዶ የማጠቃለያ ውድድሩን በአምስት ነጥብ አራተኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቋል።

06:00 በቀጠለው ሁለተኛ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማን ከፋሲል ከነማ አገናኝቶ ሀዋሳ ከነማ 2-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ውድድሩን ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ ለማጠናቀቅ ችሏል። ሀዋሳ ከነማ በወላይታ ድቻ ሽንፈት በማስተናገዱ ለዋንጫ የነበረውን ዕድል አሳልፎ መስጠቱን ተከትሎ በዛሬው ጨዋታ አሰልጣኝ ብርሃኑ ወርቁ አብዛኛውን የቡድኑን ቁልፍ ተጫዋቾችን በማሳረፍ በዚህ ውድድር ላይ ያልተጠቀሙባቸውን ተጫዋቾች በማስገባት ወደ ሜዳ በመግባት የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ አድርገዋል። በአንፃሩ በዐፄዎቹ በኩል ከዚህ ቀደም በዚህ ውድድር ላይ ካደረጉዎቸው ሦስት ጨዋታዎች በተሻለ በተደራጀ ሁኔታ መንቀሳቀስ ችለዋል። የመጀመርያው አጋማሽም ፋሲሎች ጎል አያስቆጥሩ እንጂ ጥሩ ፍሰት ያለው እግርኳስን ያሳዩበት ነበር።

ከዕረፍት መልስ በሀዋሳ በኩል ተቀይሮ በመግባት ልዩነት የፈጠረው እና ጎሎችን በማስቆጠር ጥሩ መንቀሳቀስ የቻለው ምንተስኖት እንድርያስ በ57ኛው ደቂቃ ለሀዋሳ የመጀመርያውን ጎል አስቆጥሯል። ከጎሉ መቆጠር በኃላ ሁለቱን የማጥቂያ መስመሮች በጥሩ ሁኔታ ሲጠቀሙ የዋሉት ፋሲሎች ጥረታቸው ተሳክቶ በ64ኛው ደቂቃ ተቀይሮ እንደገባ ብዙም ሳይቆይ ዓለማየው ደሳለኝ ባስቆጠረው ጎል አቻ ሆነዋል። ምናልባትም በኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የመመረጥ ዕድል ያገኛል ተብሎ የሚገመተው የዐፄዎቹ የመስመር አጥቂ ሐብታሙ አሰማረ ተጨማሪ ጎል መሆን የሚችሉ ዕድሎችን አግኝቶ አለመጠቀሙ እንጂ ፋሲሎች እንደነበራቸው ብልጫ ጨዋታውን ተቆጣጥረው መውጣት በቻሉ ነበር። የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ በመሄዱ በአቻ ውጤት ይጠናቀቀል ተብሎ ሲገመት 85ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር የተሻገረውን የፋሲል ግብጠባቂ ዳንኤል ስጦታው የሰራውን ስህተት ተከትሎ የሀዋሳው አጥቂ አምበሉ ሐብታሙ መኮንን ኳሱን በቀላሉ በመምታት ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በሀዋሳዎች 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ ሀዋሳ ከነማ የማጠቃለያ ውድድሩን ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ ማጠናቀቅ ችሏል።

08:00 የዋንጫውን አሸናፊ የሚጠቁመው የማጠቃለያ ውድድር የመጨረሻ ጨዋታ ወላይታ ድቻን ከመከላከያ አገናኝቶ መከላከያ 1–0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ከወላይታ ድቻ ጋር በነጥብ ቢስተካከልም በጎል ልዩነሱ በማነሱ የዋንጫ አሸናፊ ሳይሆን ቀርቷል።

በመጀመርያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እስከ 30 ደቂቃ ድረስ በፈጣን እንቅስቃሴ አብዝተው የማጥቃት መንገዳቸውን ወደ ቀኝ መስመር ባማጋደለ ጫና ይፈጥሩ የነበሩት ድ.ቻዎች በተደጋጋሚ ተከላካዮችን በማለፍ በቀኝ መስመር ሳጥን ውስጥ እየገባ ኳሶችን ያሻግር የነበረው አማኑኤል አሊሶ የሚልከውን ኳስ እየተቀበለ የውድድሩ ምርጥ አጥቂ መሆኑን ያስመሰከረው ታምራት ስላስ ወደ ጎል ደገፍ አድርጎ በመምታት የመከላከያው ግብጠባቂ ስጦታው አበበ በጥሩ ሁኔታ እያዳነበት እና የግቡን አግዳሚ ታከው የወጡበት ሙከራዎች ድቻዎች በተሻለ ለመንቀሳቀሳቸው ማሳያዎች ነበሩ። አልፎ አልፎ ወደ ፊት በመሄድ የጎል ዕድል ለመፍጠር ቢሞክሩም መከላከያዎች የተለየ ነገር ማሳየት አልቻሉም።

መከላከያዎች በተሻለ ብልጫ ወስደው የተጫወቱበት እና ወላይታ ድቻዎች በአንፃሩ ተዳክመው በታዩበት የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 64ኛው ደቂቃ የወደ ፊት ተስፋኛ አጥቂ መሆኑን በውድድሩ ላይ ማሳየት የቻለው አስቀድሞ በቢጫ ቲሴራ በከፍተኛ ሊጉ ዓምና ለሀላባ ከነማ ይጫወት የነበረው የመከላከያው አጥቂ መሐመድ አበራ በረጅሙ የተጣለለትን ከወላይታ ድቻ ተከላካዮች ፈጥኖ በመውጣት ከግብጠባቂው አቡሽ አበበ ጋር ተገናኝቶ አንጠልጥሎ ኳሷን ቢልካትም ያልተመጠነች ኳስ በመሆኗ በግቡ አናት ወደ ውጭ ወጥታለች። 

በተደጋጋሚ ወደ ጎል በመድረስ ሙከራ ማድረጋቸው ተሳክቶላቸው በ81ኛው ደቂቃ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ17 ዓመት በታች ቡድን ድንቅ የውድድር ጊዜ አሳልፎ ወደ ዋናው ቡድን ባደገበት ማግስት ንግድ ባንክ ክለብ መፍረሱን ተከትሎ ወደ መከላከያ ከ20 ዓመት በታች ቡድን ተቀላቅሎ በዘንድሮ ዓመት አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ዋናው ቡድን አሳድገውት በሁለቱም ቡድኖች እየተመላለሰ የሚጫወተው ሰለሞን ሙላው የጨዋታውን ማሸነፊያ ብቸኛ ግሩም ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በመከላከያ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ ምንም እንኳ መከላከያ ጨዋታውን በማሸነፍ ከወላይታ ድቻ ጋር ነጥቡን 12 በማድረስ ቢስተካከልም በሦስት የጎል ልዩነት በማነሱ ዋንጫውን ለወላይታ ድቻ ለማስረከብ ይገደድ እንጂ የውድድሩ የክብር አሸናፊ በመሆን ውድድሩን አጠናቋል። ወላይታ ድቻ የዘንድሮውን ጨምሮ አምናም የዚህ የማጠቃለያ ውድድር አሸነናፊ ሲሆን ለተከታታይ ሁለት ዓመት ባለ ድል የሆነ የመጀመርያው ቡድን አድርጎታል።

በመጨረሻም ለውድድሩ አሸናፊዎች የሽልማት አሰጣጥ ሥነ ስርዓት የተካሄደ ሲሆን በዚህም መሠረት፡-

1ኛ ወላይታ ድቻ የዋንጫ እና የወርቅ ሜዳልያ
2ኛ መከላከያ የብር ሜዳልያ
3ኛ ሀዋሳ ከተማ የነሐስ ሜዳልያ ተሸላሚ ሆነዋል።

* የስፖርታዊ ጨዋነት አሸናፊ መከላከያ መሆን ችሏል።

በቀጣይ ፌዴሬሽኑ ሊያስተካክላቸው የሚገባቸው ክፍተቶች

* ይህ ውድድር ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ የፀጥታ አካላት በየጨዋታዎቹ አለመኖራቸውና አልተከሰተም እንጂ አንድ አስከፊ ጉዳት በጨዋታው ላይ ቢከሰት የተሻለ ህክምና መስጠት የሚችሉ የቀይ መስቀል እርዳታ ሰጪ እና አንቡላንስ በየጨዋታዎቹ አለመኖራቸው ትልቅ ክፍተት በመሆኑ ለቀጣይ ሊታረም ይገባል።

* ይህ የታዳጊዎች የማጠቃለያ ውድድር እንደመሆኑ መጠን ታዳጊዎቹን የበለጠ እንዲሰሩ መነሳሳትን ለመፍጠር በመጨረሻው የመዝግያ መርሐግብር ላይ አንድም የፌዴሬሽን አመራር ተገኝቶ ውድድሩን አለመመልከቱ እና ለአሸናፊዎች ቡድን ሽልማት አለመስጠቱ ውድድሩን አድርገናል ከማለት ውጭ ለውድድሩ ክብር አለመስጠት መሆኑን የሚያሳይ በመሆኑ በቀጣይ ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገባ ነው።

በውድድሩ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ካደረጉ ተጫዋቾች መካከል፡- ምንተስኖት እንድሪያስ (ሀዋሳ ከተማ)፣ ሰለሞን ሙላው (መከላከያ)፣ ታምራት ስላስ (ወላይታ ድቻ)፣ መሐመድ አበራ (መከላከያ)፣ አበባየሁ ሀሊሶ (ወላይታ ድቻ)

© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡