“በነፃነት በመጫወት ውጤት አስጠብቀን ለመውጣት ጥረት እናደርጋለን” ሥዩም ከበደ

ፋሲል ከነማ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመልስ ጨዋታ ባህር ዳር ላይ ያስመዘገበውን የ1-0 ድል የማስጠበቅ አላማ ይዞ ነገ በአዛም ኮምፕሌክስ ስታዲየም ከአዛም ጋር ይጫወታል። የመጀመርያውን ጨዋታ ካደረገ በኋላ ቡድኑን የተረከቡት አዲሱ አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ስለ ጨዋታው፣ ስላደረጉት ዝግጅት እና ተያያዥ ጉዳዮች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

የመጀመርያውን ጨዋታ የተመለከትከው በአሰልጣኞች ቦታ ላይ ሳይሆን ከተመልካች ጋር ሆነህ ነው። የቡድንህንም ሆነ የተጋጣሚን ክፍተት እና ጠንካራ ጎን እንዴት ተመለከትከው?

ለፋሲል ከነማ ኢንተርናሽናል ውድድር ላይ ሲሳተፍ የመጀመሪያው ነው። የህዝቡ ድጋፍ እንዳለ ሆኖ እንደኔ አረዳድ ተጫዋቾች ወደ ሜዳ ሲገቡ የሥነልቦና ደረጃቸው ይሄን ኃላፊነት ለመወጣት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ይሰማኛል። ሲጀምር የነበረው ሁኔታ በተወሰነ ደረጃ እንደመቀዝቀዝ ያለ ነገር ነበረው። የኳስ ቁጥጥሩ እንዳለ ሆኖ የበለጠ ወደ ተጋጣሚ ወረዳ እየገባን ግቦችን ለማስቆጠር በምናደረገው ሂደት ላይ የበለጠ ብንበረታ ኖሮ የተሻለ ነገር። የተጋጣሚን የመከላከል አደረጃጀት የመስበር ሁኔታ ላይ ላላ ብለን ነበር። እኔ እንዳየሁት ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ጫናዎች ነበሩ። ከጨዋታው በኋላ ከቡድኑ ለምስል ትንተና የሚሆን ቪዲዮ እንዲሰጠኝ ጠይቄ ተመልክቼው ነበር። እና እሱ ላይም ይበልጥ ሁለተኛ አጋማሽ ላይ የተጋጣሚ ቡድን ጫናዎች ነበሩ። እንደዛም ሆኖ ግን ጫናውን ተቋቁሞ ውጤቱን አስጠብቆ ለመውጣት የተደረገው ነገር መልካም ነገር ነው። በመልሱ ጨዋታ ላይ የተሻለ ሆኖ ለመገኘት ስራዎችን ሰርተናል። በግልም በቡድን እየተነጋገርን ቆይተናል። እነዛን ነገሮች አስተካክለን ለመውጣት ጥረት እናደርጋለን ።

በሁለተኛው አጋማሽ የተወሰደበት ብልጫ የተወሰደበት ከምን የመጣ ይመስልሀል? የአዛሙ አሰልጣኝ ከጨዋታው በኋላ በሰጠው አስተያየትም ከሁለተኛው አጋማሽ ጥንካሬያቸው ተነስተው የመልሱን ጨዋታ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል…

እንደ ተመልካች የነበረውን ሁኔታ ስትመለከተው የመልሱን ጨዋታ ሊሸነፍ ይችላል የሚል የአብዛኛው ሰው ግምት ነው። ለኔ እንደሚታየኝ ጨዋታው ላይ የነበረው ቅንጅት እንዲሁም ተጫዋቹ ላይ ድካም እመለከት ነበር። ሪትሙን ጠብቀው የማቆየት እና ያንን ለማቆም ያደረግነው እንቅስቃሴ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ጥሩ አልነበረም። እንዲያውም ለተጋጣሚ ለአዛም የተመቻቹ ነገሮች ናቸው፤ በቀላሉ ነበር ወደ እኛ ሜዳ ሲመጡ የነበሩት። እንግዲህ ከዛ ተነስቶ የነሱ አሰልጣኝ ቡድኑን ሊገመግመው ይችላል። እኛ ደግሞ በመልሱ ጨዋታ የተሻለ ነገር ነገር እናደርጋለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። በነፃነት ተጫውተን ያን ውጤት አስጠብቀን ወይም አሻሽለን ለመምጣት ነው ጥረት የምናደርገው።

አዛሞች በሁለቱ መስመሮች በሚያደርጉት ፈጣን ሽግግሮች እንዲሁም በረጃጅም ኳሶች ፋሲልን ሲያስቸግሩ ነበር። በመልሱ ጨዋታ ይህንን ዓይነት ጥቃት ለመከላከል ምን ታስቧል? በምን አይነት አቀራረብስ ለመግባት አቅዳችኋል?

የአዛሞች የመስመር እንቅስቃሴ የጠነከረው በሁለተኛው አጋማሽ ነበር። ከዛ አንፃር የሰራናቸው ስራዎች አሉ። ይበልጥ ተጠናክረን ውጤቱን አስጠብቀን እንወጣለን ብዬ ነው የማስበው። በመሰረቱ ፋሲል በ4-3-3 አሰላለፍ ነበር ለጨዋታው የቀረበው። በአቀራረቡ አሰላለፉ ላይ ቡድኑ ወገቡ ላይ በትክክል ተዘግቷል ወይ እና እነዚህ እነዚህ ነገሮች እኛን ሊያስተምሩን የሚገቡ ናቸው። ከ4-3-3 የበለጠ የተደራጀ እና በመከላከሉም ረገድ የተሻለ የሚያደርገንን የአሰላለፍ ለውጥ ልናደርግ እንችላለን። ተጫዋቾቹ እንደሚታወቀው ከበዛብህ መለዮ በቀር ሁሉም ያሉት ናቸው። ስለዚህ ይመቸናል በምንለው መልኩ ለመቅረብ እና ለማስተካከል ስንሰራ ስለነበር በዛ መልኩ ያሉብንን ችግሮች ቀርፈን ውጤቱን ለማስጠበቅ እንጫወታለን።

ለመልሱ ጨዋታ ዝግጅት ነው ቡድኑን የተቀላልከው… ቡድኑን ለማዘጋጀት የነበረህ አጭር ጊዜን እንዴት ታየዋለህ?

እንግዲህ ከጨዋታው በኋላ እንዲያገግሙ ሁለት የእረፍት ቀናት ሰጥተናቸዋል። ከዛ በኋላ ባህር ዳር ላይ ሦስት ጊዜ ልምምድ ሰርተናል። አዲስ አበባ ላይ ደግሞ አራት ቀን በጥቅሉ ወደ 7 ቀን ነው ከነሱ ጋር የቆየሁት። በዚህ ጊዜ ተጨማሪ ነገር የማደደርግላቸው ነገር ባይኖረኝም በጥንካሬ ደረጃ የተወሰነ መሻሻል አለ ብዬ አስባለሁ። ሁለተኛ ደግሞ ተጫዋቾች በነፃነት የበለጠ ያላቸውን ነገር እንዲያደርጉ ነው ጥረት የማደረገው። እንዲያውም እዚህ የተሻለ ሆነን ከተገኝን የነሱንም ደጋፊ ቀልብ መያዝ እንችላለን የሚል ግምት ስላለ በነፃነት መጫወት አለብን። ለእያንዳዱ ነገር ጠንቃቃ መሆን እንዳለብን ተነጋግረናል። የመጀመሪያውን 10 እስከ 15 ደቂቃ ከባድ ጫና ሊፈጥሩ ስለሚችሉ ያንን ነገር ነገር መቋቋም ላይ እናተኩራለን። በተጨማሪም ለእኛ አንድ ግብ ማስቆጠር ትልቅ ዋጋ አለው። ሰለዚህ ይህን ለማሳካት እነዛን ነገሮች እየተነጋገርን እየሰራን ነው የምንገኘው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡