ቶኪዮ 2020 | “ድክመታችንን ለመቅረፍ በሰራነው ስራ ለውጥ አምጥተናል” አሰልጣኝ ሠላም ዘርዓይ

በ2020 በቶኪዮ በሚዘጋጀው ኦሊምፒክ የሴቶች እግርኳስ ማጣሪያ ጨዋታ ላይ እየተካፈለ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በሁለተኛ ዙር የመጀመርያ ጨዋታ ነገ ካሜሩንን የሚያስተናግድ ሲሆን አሰልጣኟም ስለ ጨዋታው ሀሳቧን ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፃለች።

ብሔራዊ ቡድኑ ወደ ኬንያ አምርቶ በወዳጅነት ጨዋታ 3-2 ተሸንፎ ከተመለሰ በኋላ ካሳለፍነው ሰኞ ጀምሮ በዊን ባህርዳር ሆቴል ማረፊያውን በማድረግ በዓለም አቀፉ ስታዲየም ልምምድ ሲሰራ የቆየ ሲሆን አሰልጣኝ ሰላም ዘርአይ በተለይ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገችው ቆይታ የተሻለ የዝግጅት ጊዜን እያሳለፉ እንደሆነ ገልፃለች። “የባህር ዳር ቆይታችን እጅግ ጥሩ ነው። በጥሩ መንፈስም እንድንሰራ የከተማው እና የክልሉ ፌድሬሽን እገዛ አድርጎልናል። በሄድንበት ሁሉ የባህር ዳር ህዝብ እያበረታታን ይገኛል “ብላለች።

“ሜዳው በጣም ጥሩ ነው። ለምንሰራው ነገር ሁሉ እገዛን እያደረገልን ነው።” ያለችው ሠላም የወዳጅነት ጨዋታው ክፍተትን ለመድፈን እንዳገዛትም ገልጻለች። “በኬንያው ጨዋታ ላይ የተወሰኑ ክፍተቶች ነበሩብን። ያን ክፍተት መሠረት ያደረጉ እና ይሸፍናሉ ያልናቸውን ለመድፈን በሚገባ ሰርተናል። ድክመትታችንን ለመቅረፍ በሰራነው ስራ ለውጥ አምጥናል” ብላለች።

አሰልጣኟ በስመጨረሻም ” እስከ አሁን አብሮን ያልተለየው የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎናችን እንዲሆን ጥሪን አስተላልፋለሁ።” ብላለች።

ዛሬ ብሔራዊ ቡድኑ የመጨረሻ ልምምዱን ሲሰራ ሁሉም በመልካም ጤንነት ላይ ላይ የሚገኙ ሲሆን ቅድስት ዘለቀ በትርፍ አንጀት ቀዶ ህክምና ከሳምንት በፊት ከቡድኑ ውጪ መሆኗ የሚታወቅ ሲሆን ሎዛ አበራ ወደ ማልታ በማቅናቷ ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆናቸው ተረጋግጧል። በሀዋሳ የፊዚዮቴራፒ ህክምና ስታደርግ የቆየችው አጥቂዋ ሴናፍ ዋቁማም በጉዳት መሰለፏ አጠራጣሪ ሆኗል።

ማክሰኞ ባህር ዳር የደረሰው እና በአሰልጣኝ አያይን ዲጂዮንፋ የሚመራው የካሜሩን ብሔራዊ ቡድን ጠንካራ ልምምዱን እያደረገ ሲገኝ ዛሬ 10 ሰአት የመጨረሻ ልምምዱንም አከናውኗል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡