ሪፖርት | መቐለ 70 እንደርታ ከካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ውጭ ሆኗል

የኢኳቶርያል ጊኒው ካኖ ስፖርት አካዳሚን በመልስ ጨዋታ የገጠሙት መቐለ 70 እንደርታዎች አቻ በመለያየታቸው በድምር ውጤት ከውድድሩ ውጪ ሆነዋል።

በግሩም የደጋፊዎች ድባብ በጀመረው ጨዋታ መቐለ 70 እንደርታዎች ከመጀመርያው ዙር ተሰላፊዎቻቸው ውስጥ በያሬድ ከበደ እና ታፈሰ ሰርካ ምትክ ያሬድ ብርሃኑ እና ኄኖክ ኢሳያስን ተጠቅመዋል።

ከመጀመርያው ደቂቃ አንስተው አጥቅተው ለመጫወት ድፍረት የነበራቸው መቐለዎች ለግብ የቀረበ ሙከራ ለማድረግ ብዙ ጊዜ አልወሰደባቸውም። በዚህም አማኑኤል ገ/ሚካኤል በተከላካዩ ባብሎ በርናርዶ ስህተት ያገኘውን ኳስ ለኦሴይ ማውሊ ቢያሻግረውም አጥቂው ወደ ጎል መቀየር ሳይችል ቀርቷል። ጨዋታው በተጀመረ በ11ኛው ደቂቃም አማኑኤል ከተከላካዮች መሀል ሾልኮ በመውጣት ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ግሩም ግብ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ አደርጓል።

በጨዋታው ይህ ነው የሚባል የማጥቃት ዕቅድ ይዘው የገቡ የማይመስሉት እንግዶቹ ደካማ የማጥቃት አጨዋወት ቢከተሉም በተጫዋቾች የግል ጥረት ግን ጥቂት የማይባሉ ዕድሎች ፈጥረዋል። በተለይም ሳሊፍ ዲያራ ብቻውን ይዞ ገብቶ ከመምታቱ በፊት አሌክስ ተሰማ ደርሶ ያወጣለው እና አሴጆ ከመስመር አሻግሮት ፔድሮ ኦብያንድ ሞክሮ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣበት ኳስ ይጠቀሳሉ። ከዚህ ውጪ አሴጆ ሥዩምን በግሩም ሁኔታ አልፎ ወደ ሳጥን አሻግሮት አጥቂዎች ሳያገኙት ወደ የወጣው ኳስም ጥሩ ሙከራ ነበር።

በመጀመርያው አጋማሽ በብዙ መለኪያዎች የተሻሉ የነበሩት መቐለዎችም በተለይም ከ20ኛው ደቂቃ በነበረው የጨዋታ እንቅስቃሴ ፍፁም ብልጫ ወስደው በርካታ ዕድሎችም መፍጠር ችለዋል። ከነዚህም ኦሴይ ማውሊ ከቅጣት ምት ተከላካዮች የተደረቡትን ኳስ ተጠቅሞ መትቶ ቋሚ የመለሰበት፣ ሃይደር ሸረፋ በጥሩ ሁኔታ አታሎ ሞክሮ በቀላሉ ግብ ጠባቂው የመለሰው ኳስ እና ያሬድ ብርሃኑ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ ከብዙዎቹ ጥቂቶች ናቸው።

በጨዋታው በዚህ ዓመት ከብዙ ጊዜ በኃላ በተሻለ ነፃነት ከመስመር እየተነሳ ወደ ሳጥን በመግባት እንዲጫወት የተደረገው አማኑኤል ገ/ሚካኤልም በግሉ እጅግ በርካታ ዕድሎች ፈጥሯል። በተለይም በጥሩ ግላዊ ብቃት ተከላካዮች አታሎ ያመከናት ኳስ እና በተመሳሳይ አመጣጥ ለያሬድ ብርሃኑ አሻምቶለት ተጫዋቱ በግንባሩ ያደረጋት ሙከራ በጥሩ ጎን ይጠቀሳሉ። ከነዚህ ሙከራዎች በተጨማሪ ያሬድ ብርሃኑ ከመአዝን የተሻገረችውን ኳስ ተጠቅሞ በመምታት ያደረጋት እና ግብ ጠባቂው በሚያስደንቅ ብቃት ያዳናት ሙከራም ለግብ የቀረበች ነበረች። የመጀመርያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አከባቢ ግን ቤንጃሚን በመቐለ ተከላካዮች የአቋቋም ችግር ያገኛትን ኳስ በግሩም አጨራረስ ቡድኑን አቻ አድርጓል። ባለሜዳዎቹ በመጨረሻ ደቂቃ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ሳጥን ውስጥ መጠለፉን ተከትሎ ባገኙት የፍፁም ቅጣት ምት በድምር ውጤት አቻ ለመሆን ወርቃማ እድል ቢያገኙም ኦሴይ ማውሊ መትቶት ሳይጠቀምባት ቀርቷል።

የካኖ ስፖርትን ቡድን አባላት እና አራተኛ ዳኛው ያደረጉት ዱላ ቀረሽ ንትርክን ጨምሮ በርካታ እሰጣ ገባዎችን ያስመለከተን ሁለተኛው አጋማሽ በሁሉም መለክያዎች ከመጀመርያው አጋማሽ የወረደ ነበር። አጨዋወታቸው ወደ ቀጥተኛ የቀየሩት ባለሜዳዎቹ ሙከራ ለማድረግ ቀዳሚ ነበሩ። ኤፍሬም አሻሞ በጥሩ ሁኔታ በመስመር ገብቶ አሻምቷት ተከላካዮች ተረባርበው ያወጧት ሙከራም የመጀመርያዋ ነበረች።

መቐለዎች ከመጀመርያው ሙከራ ብዙም ሳይቆዩም በሦስት አጋጣሚዎች መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር። በተለይም ጋብርኤል አህመድ ዮናስ ገረመው ከማዕዘን ያሻማለት ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ያደረጋት ሙከራ እና በተመሳሳይ አሚን ነስሩም ከማዕዘን የተሻማለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ በአግዳሚው የተመለሰበት ሙከራ እጅግ ለግብ የቀረቡ ነበሩ። ከዚህ ውጪ ኦሴይ ማውሊ ከአማኑኤል እና ከኤፍሬም በተመሳሳይ ከመስመር የተሻገሩለትን ኳሶች ተጠቅሞ ያደረጋቸው ሁለት ሙከራዎችም ይጠቀሳሉ።

ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው በ 1-1 ውጤት መጠናቀቁ ተከትሎም መቐለ 70 እንደርታዎች ከአህጉራዊው ውድድር ውጪ ሲሆኑ ካኖ ስፖርት አካዳሚም ከግብፁ ኃያል ክለብ አል አህሊ የሚገናኝ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡