ሰበታ ከተማዎች አንድ ተጫዋች ሲያስፈርሙ የአራት ተጫዋቾችን ውልም አራዝመዋል

በዝውውር መስኮቱ በስፋት ይሳተፋሉ ተብለው የሚጠበቁት ሰበታ ከተማዎች አጥቂው ፍፁም ገብረማርያምን ሲያስፈርሙ የአራት ተጫዋቾችን ውል አራዝመዋል።

ውበቱ አባተን ዋና አሰልጣኝ አድርገው ለመሾም የተስማሙት ሰበታዎች ባለፈው ሳምንት በኃይሉ አሰፋ ፣ አዲስ ተስፋዬ እና አስራት ቱንጆን ማስፈረማቸው ሲታወስ አሁን ደግሞ የአጥቂ ክፍል ተጫዋቹ ፍፁም ገብረማርያምን አስፈርመዋል። የቀድሞው የሙገር ሲሚንቶ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኤሌክትሪክ እና ወልዲያ አጥቂ ያለፈውን አንድ ዓመት ከግማሽ በመከላከያ አሳልፏል።

በቡድኑ ለተጨማሪ አንድ ዓመት ለመቆየት የተስማሙት ተጫዋቾች በከፍተኛ ሊጉ የቡድኑ ስኬታማ ጉዞ ቁልፍ ሚና የነበራቸው አራት ተጫዋቾች ናቸው። ከዚ በፊት ለአዳማ ከተማ እና ለሃዋሳ ከተማ መጫወት የቻለው ፍርድአወቅ ሲሳይ፣ የቀድሞው ፋሲል ከነማ በአምበል ታደለ ባይሳ፣ በከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ፈለክክር ውስጥ የነበረው ኢብራሂም ከድር እና ባለፈው ዓመት ተስፋ ያለው እንቅስቃሴ ያሳየው አምበሉ ጌቱ ኃይለማርያም በቀጣዩ የውድድር ዓመት በሰበታ ይቀጥላሉ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡