ወልዋሎ ሦስት ተጫዋቾች አስፈርሞ አምስት ተጫዋቾችን ወደ ዋናው ቡድን አሳድጓል

በዝውውር መስኮቱ በስፋት የተሳተፉት ወልዋሎዎች አሁን ደግሞ ላለፉት ሦስት ቀናት ሙከራ ላይ የነበሩት ተጫዋቾች እና አምስት ታዳጊዎችን ወደ ቡድናቸው ቀላቅለዋል።

የሙከራ ዕድል ተሰጥቷቸው በዛሬው ዕለት ፊርማቸውን ያኖሩት ካርሎስ ዳምጠው፣ ጠዓመ ወልደ ኪሮስና ክብሮም ዘርዑ ናቸው። ከወልዋሎ ሁለተኛ ቡድን አድገው ላለፉት ዓመታት ከአክሱም ከተማ እና ሶሎዳ ዓድዋ ቆይታ ያደረጉት እና ከአንድ ወር በፊት ሶሎዳ ዓድዋ ወደ ከፍተኛ ሊጉ ሲያድግ ጥሩ ብቃታቸውን ያሳዩት ጠዓመ (ፎቶ- በቀኝ) እና ክብሮም (ፎቶ – መሐል) አሳዳጊ ክለባቸውን በድጋሚ ለማገልገል ፊርማቸው አኑረዋል።

ሦስተኛው የቡድኑ ፈራሚ አጥቂ ካርሎስ ዳምጠው (ፎቶ – ግራ) ሲሆን ከጅማ አባ ቡና ጋር በግሉ ጥሩ የውድድር ዓመትን ነበር ያሳለፈው። በባለፈው ዓመት የጅማ አባቡና ቆይታው ስምንት ግቦች ያስቆጠረው ይህ የቀድሞ የነገሌ አርሲ፣ መከላከያ እና መቐለ 70 እንደርታ ተጫዋች ከአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ጋር ዳግም የመስራት እድልም አግኝቷል።

በተያያዘ ዜና ባለፉት ቀናት ሠላሳ ለሚደርሱ ወጣት ተጫዋቾች የሙከራ ዕድል የሰጡት ወልዋሎዎች አምስቱን ወደ ዋናው ቡድን አሳድገዋል። ዮሴፍ ኃይለማርያም፣ ኄርሞን ጉዕሽ፣ ስምዖን ሐጎስ፣ ነጋሲ ገብረየሱስ እና ናትናኤል ኪዳነ ወደ ዋናው ቡድን ያደጉ ተጫዋቾች ናቸው።

ባለፈው የውድድር ዓመት ሰመረ ሃፍታይ ፣ ስምዖን ማሩና ሽሻይ መዝገቦ ወደ ዋናው ቡድን ያሳደጉት ቢጫ ለባሾቹ በዚ ዓመት ደግሞ ሌሎች አምስት የታዳጊ ቡድን ቡድን ተጫዋቾች ወደ ቡድኑ በመቀላቀል በወጣቶች ላይ የጀመሩት ስራ አስቀጥለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ