ቶኪዮ 2020 | “ጎሎች ለማስቆጠር እንጫወታለን” አሰልጣኝ ሠላም ዘርዓይ

ከሳምንት በፊት ባህር ዳር ላይ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ሁለተኛ ዙር ማጣርያ ካሜሩንን በመጀመርያ ጨዋታ የገጠሙት ሉሲዎቹ 1-1 መለያየታቸው ይታወሳል። ዛሬ ያውንዴ በሚገኘው አህመድ አሂዲጄ ስታዲየምም የመልስ መርሀ ግብራቸውን የሚያደርጉ ይሆናል።

ቡድኑ በዛሬው ዕለት ጨዋታውን ከማድረጉ በፊት ቡድኑ ስላደረገው ዝግጅት አሰልጣኝ ሰላም ዘርአይ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠችው አስተያየት “ዛሬ ነው ሥራችንን የምናሳየው፤ በተወሰነ መንገድ ተሻሽለናል። ከባድ ጨዋታ ቢሆንም በሜዳ ላይ ማድረግ ያለብንን እናሳያለን።” ብላለች። አሰልጣኛ አክላም የሎዛ አበራ አለመኖር ቡድኑን እንደጎዳ ገልፃለች፡፡ “የሎዛ አለመኖር ትልቅ አቅም ነው የቀነሰው። እሷ ኖራ ቢሆን ጥሩ ነገር ይኖረን ነበር።”

በባህር ዳሩ ጨዋታ ደክማ የታየችው ሴናፍ ዋቁማን አቋም ለማሻሻል እንደሰሩ የገለፀችው እንደቡድን የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ድክመት እንደነበረበት ገልፃለች። “የሴናፍ ስህተት ጎልቶ ይውጣ እንጂ የነበሩት ተጫዋቾችም ተመሳሳይ ነበሩ። ዞሮ ዞሮ እንደቡድን ማጥቃቱ ላይ ስህተት ነበረብን። ይህን አርመን የተሻለ ቡድን ቡድን እናያለን የሚል ግምት አለኝ። ተደጋጋሚ ጨዋታ ማድረጋችን ደግሞ እንድንሻሻል ይረዳናል።” ብላለች።

ሜዳው አመቺ እንደሆነ የምትናገረው የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ተመሳሳይ አየር በመኖሩ ጨዋታው ላይ ችግር እንደማይፈጥርባቸው ገልፃ ጎል ማስቆጠር ላይ ትኩረት አድርገው ወደ ጨዋታው እንደሚገቡ ገልፃለች። “አየሩ ከኛ ጋር ተመሳሳይ ነው፤ ሜዳውም ምቹ ነው። በጨዋታው ከማሸነፍ እና ግብ አስቆጥሮ አቻ ከመለያየት ውጪ አማራጭ የለንም። ጎል ማግባት ብቻ ነው ወደ ቀጣዩ ዘር የሚያሳልፈን። ስለዚህ ጎል ለማስቆጠር ነው የምንጫወተው።” ብላለች።

ዛሬ 11;30 በሚጀምረው ጨዋታ አሰልጣኛ የተወሰኑ ለወረጦች አድርጋ ወደ ሜዳ እንደምትገባ ሲጠበቅ ከብርቱካን ገብረክርስቶስ አጠራጣሪ ጉዳት ውጪ ሴናፍ ዋቁማ ሰሞኑን ከነበረባት ጉዳት ማገገሟን እና ሌሎቹ የቡድን አባላትም በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ገልፃለች፡፡

ዛሬ 11:30 የሁለቱም ብሔራዊ ቡድን የመልስ ጨዋታ የሚከናወን ይሆናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ