አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ከምዓም አናብስት ጋር ይቆያሉ

ባለፉት ቀናት የፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮኖቹን ለመልቀቅ ጥያቄ ያቀረቡት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ከክለባቸው ጋር እንደሚቆዩ ተገለፀ።

ከጥቂት ቀናት በፊት አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ ለክለባቸው የሚስተካከሉ ቅድመ ሁኔታዎች በማስቀመጥ የመልቀቂያ ጥያቄ እንዳቀረቡ መዘገባችን ይታወሳል። አሁን ደግሞ ከአሰልጣኙ ባገኘነው መረጃ አስተዳደራዊ ጉዳዮች እንዲስተካከሉ የጠየቋቸው ጥያቄዎች ክለቡ እንዲያስተካክል ፍቃደኛ መሆኑን ገልፀው ከክለቡ ጋር ለመቀጠል እንደወሰኑ ተናግረዋል። “እንዲስተካከሉ የጠየቋቸው በርካታ ጥያቄዎች ነበሩ። ክለቡም ያቀረብኳቸው ቅድመ ሁኔታዎች በሙሉ ፍላጎት ለማስተካከል ፍቃደኛ በመሆኑ በስራዬ ለመቀጠል ወስኛለው ብለዋል።”

አሰልጣኝ ገብረመድህን ጨምረው እንደገለፁት በደጋፊዎች ዙርያ ያነሱት ቅሬታ ጥቂቶችን እንጂ ሙሉውን ደጋፊ የማይወክል እንደሆነ ገልጸዋል። “ከደጋፊዎች መጣ የተባለው ነገር ሁሉም ደጋፊን አይወክልም። በርካታ ድጋፋቸው የገለፁልን ደጋፊዎቻችንም ነበሩ፤ ይህ ደግሞ በእግር ኳስ ላይ ያለ ነገር ነው። ክለባችንን ለማጠናከር በእንቅስቃሴ ነው ስለምንገኝ ቀጣዩ ዓመትም ደጋፊዎቻችንን የምናስደስትበት ይሆናል” ብለዋል።

ናይጄርያዊው አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢን ያስፈረሙት ምዓም አናብስት በቀጣይ ቀናትም ተጫዋቾች ለማስፈረም እንቅስቃሴ መጀመራቸው ሲታወቅ የቅድመ ውድድር ዝግጅትም በቅርብ ቀናት የሚጀምሩ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ