የአሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ ጋዜጣዊ መግለጫ (ዝርዝር ዘገባ)

አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ በዛሬው ዕለት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ አተኩረው ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠታቸው ይታወቃል። የመግለጫው ዋና ዋና ሃሳቦችንም በሚከተለው መልኩ ይዘን ቀርበናል።

– አስገቡት ስለተባለው የመልቀቂያ ደብዳቤ

በመጀመርያ መቐለ 70 እንደርታ የሚል የክለቡ ያልሆነ ሃሰተኛ የፌስቡክ ገፅ ያለው ነገር ትክክል አይደለም። ከነሱ ጋር ያደረጉት ቆይታም ሆነ የሰጠሁት ምላሽ አልነበረም። ባለፈው ዓመት በርካታ ችግሮች አሳልፈናል፤ በዛ ምክንያት ደግሞ እንዲስተካከሉ ያቀረብኳቸው በርካታ ጥያቄዎች አሉ። ከክለቡ ጋር የምንቀጥል ከሆነ የባለፈው ዓመት ችግሮቻችንን መፈታት አለባቸው። እንደ ቡድን ለመቀጠል ቡድናችን ማጠናከር እና ማስፈረም አለብን ብዬ ጥያቄ አቅርቤ ነበር።

ከዛ ባለፈ የቴክኒክ ቡድኑ ይስፋ ቴክኒካል ዳይሬክተርም ይቀጠር በታዳጊዎች ላይ መስራት አለብን ብዬ ጥያቄ አቅርቤያለው። በአጠቃላይ ሲታይ ብዙም ችግር የለም፤ ግን ደግሞ ምንም ችግር የለም ማለት አይደለም። ባለፈው ዓመት ችግሮች ነበሩብን፤ በአፍሪካ ውድድር እንደፈለግነው መሄድ አልቻልንም፤ በተወሰኑ ደጋፊዎች የተፈጠሩ ችግሮች ነበሩ፤ ግን በትምህርት የሚስተካከል ነገር ስለሆነ ይህ እንደ ትልቅ ነገር መታየት የለበትም። ሌላው አንዳንድ የደጋፊ ማኅበር አባላት ሆነው ለመጥፎ ስራዎች ሲቀሰቅሱ ነበር፤ ይሄም እንዲስተካከልልኝ ጠይቄያለው።

– ለክለቡ ስላቀረባቸው ዋና ዋና ጥያቄዎች

በደብዳቤ ላቀረብኳቸው ጥያቄዎች ቶሎ ምላሽ አይሰጠኝም። ጥያቄዎች አንስቼ ቶሎ ምላሽ አልተሰጠኝም። እንደ ምሳሌ የአሞስ ጉዳይ ብናነሳ ሳይጫወት ነው ዓመቱ ያስለፈው። ጉዳት ስለነበረበት በብዙ ጥረት አሳከምነው። ከጉዳቱ ነፃ ሆኖ እያለ ግን ትልቅ የዲስፕሊን ችግር ነበረበት። ይህ በአፋጣኝ እንዲፈታ ጠይቄ ግን አልሆነም። ሌላው በዓመቱ መጀመርያ ወደ ዋናው ቡድን ያሳደግናቸው ሶስት ተጫዋቾች ነበሩ። የሚያስፈልጋቸው ነገር ይሟላላቸው ብዬ ጠይቄ መሟላት አልቻለም። ታዳጊዎች ናቸው፤ ብዙ ነገርም ያስፈልጋቸዋል ብዬ አስቤ ጥያቄ አቅርቤ ነበር።

ሌላው የተጫዋቾች ካምፕ ላይ የሚፈጠሩ ችግሮች ነበሩ። ለምሳሌ በየግዜው የትጥቅ መጥፋት ያጋጥሙ ነበር ይሄም በግዜው ይፋታ የሚል ጥያቄ አቅርቤ መፈታት አልቻለም።

ከዛ በተጨማሪ ሽልማት አሰጣጥ ላይ ያቀረብኳቸው ጥያቄዎች ነበሩ። ሽልማት አሰጣጡ ሚዛናዊ አደለም ይህም በብዙዎች ቅሬታ ፈጥሯል። እነዚን ጥያቄዎች አቅርብያለው በስራዬ ቀጥዬ እነዚን ችግሮች እንዲፈቱ እጥራለው።

– ስለ ታዳጊ ቡድን እና ስለቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች

በረጅም ጊዜ ታዳጊዎች ላይ መስራት እንፈልጋለን። በቀጣይ የውጭ ተጫዋቾች ቀንሰን ለራሳችን ተጫዋቾች ዕድል እንሰጣለን በረጅም ጊዜ ታዳጊዎች ላይ መስራት ላይ እንፈልጋለን። የውጭ ተጫዋቾች መቀነስ አስበን የነበረ ቢሆንም በዚህ ዓመት በአንዳንድ ምክንያቶች አልሆኑም። በቀጣይ ግን እነዚህን እየቀነስን ለከተማው ታዳጊዎች በስፋት ዕድል እንሰጣለን።

ሌላ ሊነሳ የሚገባው ጉዳይ የተወሰኑ ተጫዋቾች ቆይታ ጥያቄ ምልክት ላይ ነው። የአማኑኤል ገ/ሚካኤል ጉዳይ አለ፤ አንዳንድ ክለቦች ከኛ የተሻለ ገንዘብ እንዳቀረቡለት እናውቃለን። ይህ ደግሞ ለኛ ትንሽ ያስቸግረናል። ለአንድ ተጫዋች ስድስት እና አምስት ሚልዮን ማውጣት ከክለቡ የፋይናንስ አቅም አንፃር በጣም ከባድ ነው። የፊሊፕ ኦቮኖ ጉዳይም አለ እሱም ሌሎች ቡድኖች የተሻለ ነገር አቅርበውለታል። ከብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎች መልስ ቡድኑን እንዲቀላቀል በግል ነግሬዋለው የሱም ቆይታ በቅርቡ ይታወቃል። ክለባችን ግን ተጫዋቾቹን ለማቆየት እስከ መጨረሻው ደረጃ ድረስ ጥረት ያደርጋል። ቡድኑ ግን ተወዳዳሪ ለመሆን በስታፍም በሌላም ረገድ ለውጥ ያስፈልገዋል።

* አሰልጣኙ ከጋዜጠኞች ለተጠየቁት ጥያቄዎች የሰጧቸው ምላሾች

– ስለፈረሰው የ ‘ B’ ቡድን

ገብረመድህን ሲመጣ ነው ሁለተኛው ቡድን የፈረሰው የሚል ነገር አለ። ሆኖም አንዳንድ ጥቅማቸው የጎደላቸው ሰዎች ናቸው እንደዛ የሚል መረጃ የሚሰጡት። ትራንስ በገ/መድህን ኃይሌ ነው የፈረሰው የሚልም ሌላ ነገር አለ። ያፈረሰው መጠየቅ እያለበት እዚ ጉዳይ ላይ የኔ ስም መነሳት የለበትም። እኔ ከለቀቅኩ በኃላ ቡድኑ ቡድኑ በውድድርም ነበር እኮ።

ይህ የመቐለ 70 እንደርታ ‘ B’ ጉዳይም ተመሳሳይ ነው። ሁለተኛ ቡድን አለ ብዬ ጠይቄ ነበር፤ የተሰጠኝ ምላሽ ግን ፈርሷል የሚል ነበር ምክንያቱም ዕድሜ ጉዳይ ነው ተባልኩ። ሃዋሳ የመጨረሻ ውድድር (አንደኛ ሊግ ማጠቃለያ) ነበር፤ እዛ እየተወዳደሩ ስለ ነበር ወደ ቦታው ሄጄም አይቻቸዋለው። በዛም ነው 3 ተጫዋቾች ወደ ዋናው ያሳደግኩት።

– ስለ ፊሊፕ ኦቮኖ እና አማኑኤል ገ/ሚካኤል

ስለሚጠቅሙን ቢመጡ ጥሩ፤ ግን የተጠየቁት ቅድመ ሁኔታዎች በጣም በጣም ከባድ ናቸው።
ኦቮኖ እዛ ሆኖ መደራራደር ጀምሯል። መልሱን በቀጣይ ጊዜያት የምናየው ይሆናል። ይገባዋል አገልግሎናል ክለባችን ቤቱ ነው ብለን በርካታ ወጪ አውጥተን አሳክመነዋል። አሁን እየሆነ ያለው ግን ሌላ ነው። ቢመጡ ጥሩ ነው። ወሳኝ ተጫዋቾች ናቸው፤ ደጋፊም ይወዳቸዋል፤ ውላቸውን ያራዝማሉ ብዬም አስባለው።

– ስለ ሽልማት ጉዳይ ያለው ቅሬታ

የሽልማት በርካታ ጥያቄዎች አሉ ፤ ለክለቡ ጥያቄዎቹ አዲስ ነው የሆነባቸው ግን ጥያቄው የኔ አይደለም፤ የሁሉም ነው። ጥያቄውም የሚዛናዊነት ጥያቄ ነው። ትናንትና ከክለባችን ፕሬዝዳንት ተነጋግረን ነበር ። የጠየቅኩት እንደሚሟላ ቃል ገብቶልኛል። የቅድመ ውድድር ዝግጅቱ በጥሩ ሁኔታ እንድንጀምር ትጥቅ እንዲሟላም ጠይቄያለው።

ስለ ወቅታዊ የዝውውር ጉዳይ

ህጉን ተከትለን እንሄዳለን። ተጫዋች በ50 ሺህ አይመጣም፤ ይህ ግልፅ ነው። ሁሉም ክለቦች እየሄዱበት ያለው መንገድም ግልፅ ነው። መጀመርያ ይሄ እስኪስተካከል ብለንም ጠብቀም ነበር። በጉዳዩ ሁሉም ቡድኖች ላይ ጥያቄዎች አሉ። ግን አንዳንድ ደጋፊዎች የተወሰነ የቦነስ ጭማሪ እንደሚሸፍኑልን ገልፀውልናል። በዛ መንገድም እየሰራን ነው፤ በዛም ጥሩ ነገር አለ።

ስለ ቡድኑ ከፍተኛ ተከፋዮች

በአንዳንድ ተጫዋቾች ሳንጠብቀው የብቃት መውረድ አለ። እዚህ መጥተው ሳንጠብቃቸው የወረዱ ተጫዋቾች አሉ። ከፍተኛ ተከፋዮች ስለ ሆኑም ከነሱ ጋር በስምምነት ለመለያየት እየሰራን ነው።

– በችግሮቹ ያቀረብከው ጥያቄ በጎ ምላሽ ባይሰጥህ ክለቡን ትለቅ ነበር?

አሁን ላይ ሆኜ እንዲህ ነው እንዲህ ነው ብዬ መናገር አልችልም። ባይፈቱ የሚሆነው ነገር ግልፅ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ