ዋሊያዎቹ በመጨረሻም ኢትዮጵያ ገብተዋል

ላለፉት ቀናት በሌሶቶ ጥሩ ያልሆነ ቆይታ የነበራቸው ዋሊያዎቹ ከደቂቃዎች በፊት በሠላም አዲስ አበባ ገብተዋል።

ከጥቂት ቀናት በፊት ለኳታር የዓለም ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ ሌሶቶን ለመግጠም ወደ ማሴሩ አምርተው እሁድ ዕለት ጨዋታውን ካካሄዱ በኋላ በተፈጠሩ የአሰራር ክፍተቶች በሀገሪቱ ለመቆየት ተገደው የብዙዎች መነጋገርያ ሆነው የነበሩት ዋሊያዎቹ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ቦሌ አየር ማረፍያ ደርሰዋል።

ከጨዋታው በኋላ ከትኬት ጋር በተያያዘ የፌዴሬሽኑ የአሰራር ክፍተት እና በአየር ማረፍያ በተፈጠረው መስተጓጎል በአየር ማረፊያው ወንበሮች ላይ ለማደር ተገደው የነበሩት የብሔራዊ ቡድኑ አባላት ከሰዓታት በኋላ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል የእራት ግብዣ እንደሚደረግላቸው ለማወሽ ተችሏል።

ፌደሬሽኑ ከአንድ ቀን በፊት ጉዞው አስመልክቶ እና ስለተፈጠረው ሁኔታ ለብዙዎች ግልፅ ያልሆነ ማብራሪያ በይፋዊ ድረ ገፁ መስጠቱ ይታወሳል።


© ሶከር ኢትዮጵያ