ሐይደር ሸረፋ ፈረሰኞቹን ለመቀላቀል ተስማማ

ባለፈው ዓመት በሊጉ ድንቅ አቋም ካሳዩ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የነበረው የመቐለ 70 እንደርታው አማካይ ሐይደር ሸረፋ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ፊርማውን ለማኖር ተስማምቷል።

የከፍተኛ ሊጉ ጅማ አባ ቡናን ለቆ መቐለ 70 እንደርታ ከተቀላቀለ በኋላ ከቡድኑ ጋር በቶሎ በመላመድ ቡድኑ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ የሊጉን ዋንጫ እንዲያነሳ ከፍተኛ ድርሻ የነበረው ተጫዋቹ በቀጣይ ጥቂት ቀናት በይፋ የፈረሰኞቹ ንብረት ይሆናል።

ለደደቢት፣ ጅማ አባቡና እና መቐለ 70 እንደርታ መጫወት የቻለው አማካዩ በ2007 በአሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ አማካኝነት ለኦሊምፒክ ብሔራዊ ቡድን ጥሪ ተደርጎለት መጫወቱ ሲታወስ በዚህ ዓመት አጋማሽም ለዋናው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግልጋሎት መስጠት ጀምሯል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሐይደር ቀደም ብሎ የደደቢቶቹ አማካዮች የአብስራ ተስፋዬ እና አቤል እንዳለ እንዲሁም የወልዋሎው ተከላካይ ደስታ ደሙን የግሉ ማድረጉ ይታወሳል።


© ሶከር ኢትዮጵያ