ወልቂጤ ከተማ እና ማፍሮ ስፖርት የውል ስምምነት ፈፀሙ

አዲስ አዳጊዎቹ ወልቂጤ ከተማዎች ማፍሮ ስፖርት ከተሰኘ ዓለምአቀፍ ትጥቅ አቅራቢ ኩባንያ ጋር ለሁለት ዓመታት የሚቆይ የአጠቃላይ ትጥቆች ለማቅረብ የሚያስችል የውል ስምምነት በዛሬው ዕለት በብሉ ስካይ ሆቴል ተፈራርመዋል፡፡

በፊርማ ሥነስርዓቱ ላይ የወልቂጤ ከተማ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የክለቡ አዲሱ ተሿሚ ዋና አሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው እንዲሁም የማፍሮ ስፓርት ዋና ስራ አስፈፃሚ መሐመድ ጋምዳ ተገኝተዋል፡፡

መርሃግብሩን በንግግራቸው የከፈቱት የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ታምራት ሲሆኑ በንግግራቸውም ስምምነቱ በፕሪምየር ሊግ የሚካፈለው ዋናው ቡድን በሜዳውና ከሜዳው ውጭ ከሚለብሳቸው መለያዎች በተጨማሪ ቡድኑ በቅርቡ ስራ ወደ ሥራ የሚያስገባው የተጫዋቾች አካዳሚ ለሚገቡ ተጫዋቾች እንዲሁም የአሰልጣኝ ቡድን አባላት የሚሆኑ ትጥቆችን በሙሉ የሚያካትት ስምምነት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በመቀጠል ንግግር ያደረጉት የክለቡ ም/ፕሬዘዳንት አቶ አበባው ሰለሞን ሲሆኑ በንግግራቸውም ወልቂጤ ከተማ ለለውጥ እየተጋ የሚገኝ ክለብ መሆኑን አውስተው ይህም ስምምነት ክለቡ በስፋት እየሄደበት ከሚገኘው ክለቡን የማዘመንና የክለብ ቁመና ለማላበስ የሚደረገው ጥረት አካል መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በማስከተል የማፍሮ ስፖርት ዋና ስራ አስፈፃሚ መሐመድ ጋምዳ በአፍሪካ ላይ በተሻለ መልኩ ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ የሚገኘው ኩባንያቸው በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን ስምምነት በመፈፀሙ የተስማቸውን ደስታ ገልፀው፤ እንደ ወልቂጤ ከተማ ዓይነት በግልጽ የተገመጠ ግብን ታሳቢ አድርጎ ከሚሰራ ክለብ ጋር መስራታቸው የፈጠረባቸውን ደስታን ገልፀዋል። አያይዘውም ድርጅታቸው በቀጣይም ከሌሎች የኢትዮጵያ ክለቦች ጋር ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውንና የክለቦችን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ ሁኔታ በጋራ ለመስራት በራቸው ክፍት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ቀጥለው በክረምቱ ክለቡን በዋና አሰልጣኝነት የተረከቡት አሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው ክለባቸው በአዲሱ የውድድር ዓመት ጅማሮ መሠል ዘመናዊ አካሂዶችን ለመከተል በመንቀሳቀሱ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረው ሂደቱም በሜዳ ላይ ለሚኖረው ውጤት ዓይነተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ገልፀዋል፡፡


በመቀጠል ክለቡን በክረምቱ የዝውውር መስኮት የተቀላቀሉት ቶማስ ስምረቱ፣ ኤፍሬም ዘካሪያስ፣ ይድነቃቸው ኪዳኔ እና የቡድኑ ነባር ተጫዋች የሆነው አብዱልከሪም ወርቁ ቡድኑ በቀጣይ የውድድር ዘመን በሜዳውና ከሜዳው ውጪ የሚጠቀምባቸው የሜዳ ተጫዋቾች እንዲሁም የግብጠባቂዎች መለያ በመልበስ አስተዋውቀዋል፡፡

በማስከተል የወልቂጤ ከተማ ም/ፕሬዝዳንት አቶ አበባው ሰለሞንና የማፍሮ ስፖርት ዋና ሥራ አስፈፃሚ መሐመድ ጋምዳ መካከል የውል ስምምነት የተፈራርመ ሲሆን ለማሳያነት የተሰሩ መለያዎችንም በይፋ ርክክብ ፈፅመዋል፡፡

በመጨረሻም በስየሥፍራው ከተገኙ የመገናኛ ብዙሃን አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች የክለቡ ም/ፕሬዚዳንት ምላሽ ሰጥተዋል፤ ከተወሰኑት በጥቂቱ፡-

ማፍሮ ስፖርትን ስለመረጡበት ምክንያት

“ማፍሮን ከመምረጣችን በፊት ለጊዜው ስማቸውን መጥቀስ ከማልፈልጋቸው ከተለያዩ ተቋማት ጋር ግንኙነቶችን አደርገናል፤ ነገር ግን በስተመጨረሻ ከዋጋ እና ጥራት በተጨማሪ ኩባንያው ሙሉ ትጥቆቹን በስድስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ በእጃችን እንደሚያስገባ ስለተስማማን ማፍሮን ልንመርጥ ችለናል፡፡”

ስለቀጣይ ዓመት እቅዳቸውና እያስገነቡ ስለሚገኙት አካዳሚ

” በ2012 የውድድር ዘመን አዲስ ወደ ሊጉ እንደማደጋችን ዋነኛ አላማችን በቀጣዩ የውድድር ዘመን በሊጉ መቆየት ነው፡፡ እያስገነባን የምንገኘው የእግርኳስ አካዳሚ በአሁኑ ወቅት ወደ 96% በሚሆን መልኩ ተጠናቋል፤ በአሁኑ ወቅት የሚቀረን የአጥር ግንባታና የውስጥ መገልገያ ቁሶች ብቻ ናቸው። በቀጣይ ጥቂት ጊዜያት ውስጥ የተጫዋቾች ምልመላ ቡድን አዋቅረን ከአንድ እስከ ሁለት ወር ባለው ጊዜ ውስጥ አካዳሚውን ወደ ስራ የምናስገባ ይሆናል፡፡”


© ሶከር ኢትዮጵያ