የሴቶች ዝውውር | አዳማ ከተማ ሁለት ተጫዋቾችን አስፈርሟል

የአምናው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን አሸናፊው አዳማ ከተማ የመከላከያዎቹ የመስመር አጥቂዎች ብሩክታዊት ብርሀኑ እና የምስራች ላቀውን አስፈርመዋል፡፡

በክረምቱ የዝውውር መስኮት እምብዛም በንቃት እየተሳተፉ የማይገኙት አዳማ ከተማዎች በቅርቡ ወደ ማልታው ቢርቢካራ ባመራችው ሎዛ አበራና በተመሳሳይ ወደ ስዊድን ታቀናለች ተብላ የምትጠበቀውን ሴናፍ ዋቁማን ለመተካት በማሰብ ክለቡ ሁለቱን የመስመር አጥቂዎችን ለማስፈረም ተስማምተዋል፡፡

የቀድሞዋ የአርባምንጭ ከተማና መከላከያ ተጫዋች የምስራች ላቀው በሊጉ ደምቀው መውጣት ከቻሉ ተጫዋቾች ውስጥ አንድዋ ስትሆን ሌላኛዋ የክለቡ አዲስ ፈራሚ የሆነችው ታታሪዋ የመስመር አጥቂ ብርኩታዊት ብርሀኑ ባላፉት ዓመታት በወጥ ብቃት ቡድኗን ማገልገል ችላለች፡፡

የክለቡ አሰልጣኝ ሳሙኤል አበራ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት በቡድኑ ውስጥ ከሚገኙት 26 ተጫዋቾች ውስጥ ቡድኑ በቀጣይ የውድድር ዓመት ከበጀት ቅነሳ ጋር በተያያዘ ቁጥራቸውን ወደ 20 ዝቅ የማድረግ ግዴታ ውስጥ ስለመግባታቸው ገልጿል፤ በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናትም ይህ ጉዳይ እልባት ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በተመሳሳይ ክለቡ በቀጣዮቹ ቀናት ውስጥ አንድ ወይም ሁለት ተጫዋች ሊያስፈርም እንደሚችል ለማወቅ ተችሏል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ