ወላይታ ድቻ አማካይ ተጫዋች አስፈርሟል

በርከት ያሉ ነባር ተጫዋቾች ውል ያላቸው በመሆኑ በዝውውር ሂደቱ ብዙም ተሳትፎ ያላደረገው ወላይታ ድቻ ተመስገን ታምራትን ዛሬ አስፈርሟል፡፡

ከሀዋሳ ከተማ ኮረም ሰፈር እግር ኳስን በመጫወት የጀመረው ይህ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች በሀዋሳ ከተማ ከ17 እና 20 ዓመት ቡድኖች ውስጥ ተጫውቶ ከማሳለፉም ባለፈ በኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድን ውስጥም በአሰልጣኝ አጥናፉ ዓለሙ ተመርጦ መጫወት ችሏል፡፡ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በደቡብ ፖሊስ ቆይታን ያደረገው ተመስገን በሁለተኛው ዙር በቡድኑ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ተመራጭ የነበረ ቢሆንም ከቴሴራ ጋር በተያያዘ መጫወት ሳይችል ቀርቶ እንደነበርና አሰልጣኙም በሁኔታው ቁጭት አድሮባቸው እንደነበር ለሶከር ኢትዮጵያ የተናገሩ ሲሆን አሁን በወላይታ ድቻ ተገናኝተዋል።

ድቻዎች የአማካይ ስፍራ ተጫዋች የሆኑትን ሰለሞን ወዴሳ እና ዘላለም ኢሳይያስን ከክፍያ ጋር መስማማት ሳይችሉ በመቅረታቸው ዝውውራቸውን ሳያጠናቅቁ መቅረታቸው ሲታወስ ይግረማቸው ተስፋዬ ከተመስገን ታምራት ቀደም ብሎ የፈረመ ተጫዋች ነው፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ