ደቡብ ፖሊስ ተመስገን ዳናን በይፋ አሰልጣኝ አድርጎ ሾመ

በዐምናው የውድድር ዘመን ከፕሪምየር ሊጉ የወረደው እና የፎርማት ለውጡን ተከትሎ በድጋሚ ወደ ሊጉ የተመለሰው ደቡብ ፖሊስ ተመስገን ዳናን በይፋ የክለቡ ዋና አሰልጣኝ አድርጎ መቅጠሩን ዛሬ በክለቡ ፅህፈት ቤት በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የክለቡ አዲስ ተሿሚ ፕሬዝዳንት አቶ ታሪኩ ኡጋሞ፣ የክለቡ ሥራ-አስኪያጅ ኮማንደር ግርማ ዳባ፣ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዋ ኢንስፔክተር እታገኝ ዜና እንዲሁም አዲሱ አሰልጣኝ ተመስገን ዳና እና ሌሎች የክለቡ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ረጅም ዓመታትን የክለቡ ፕሬዝዳንት በመሆን ሲመሩ የነበሩት ኮማንደር ዳንኤል ገዛኸኝ በጡረታ መሰናበትን ተከትሎ የደቡብ ፖሊስ ፕሬዝዳንት በመሆን የተሾሙት የቀድሞ የሀዋሳ ከተማ ክለብ ፕሬዝዳንት አቶ ታሪኩ ኡጋሞ ስለ አዲሱ አሰልጣኝ ሹመት በተመለከተ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግራቸው ነበር ፕሮግራሙ የጀመረው። ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው “በዋናነት አሰልጣኙ በታዳጊዎች የሚያምን በመሆኑና ይህንንም በቁርጠኝነት ተግባራዊ ለማድረግ በሚያደርገው ጥረት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ወጣት አሰልጣኝ በመሆኑ ልንመርጠው ችለናል። ከውጤታማነትም አንፃር ክለቡን ወደ አንድ ምዕራፍ ከፍ ያደርጋል የሚል እምነት ስላለን ነው እሱን የመረጥነው። ብለዋል።

በመቀጠል የክለቡ ሥራ-አስኪያጅ ኮማንደር ግርማ ዳባ ባደረጉት ንግግር “ይህ ክለብ እጅግ በርካታ ስፖርቶኞችን እና አሰልጣኞችን ማፍራት ችሏል፡፡ የበርካታ ታዳጊ ልጆችም ማፍለቂያ ነው። ሠራዊታችን ከሚሰራው የፀጥታ ስራ ባለፈ እንደዚህ ወጣቱን የሚደግፍ እና ሠራዊቱንም ከህዝቡ የሚያገናኝ ሲሆን ከአገናኝ ድልድዮቹ መካከል ደግሞ ስፖርቱ አንዱ ነው። ክለባችን በእግር ኳሱም ብቻ ሳይሆን በሌሎች የክለቡ በያዛቸው የስፖርት ዓይነቶች በተለይ በአትሌቲክሱ ውጤታማ ስፖርተኞችን ለኢትዮጵያ አበርክቷል። እግር ኳስ ክለቡን ወደቀደመው ማንነቱ ለመመለስ እና ለእኛም ሆነ ለሠራዊቱ ትልቅ ደስታን ለመፍጠር ተዘጋጅተናል። ለ2012 የውድድር ዓመት ክለቡ የተሻለ እና ውጤታማ የሆነ ውጤት የሚያስመዘግብበት መንገድ ለመክፈት ተግተን በመስራት ለክለባችንም ሆነ ለሀገር ጥሩ ተጫዋቾችን እናወጣለን።” ብለዋል።

በመቀጠል የክለቡ የቦርድ አባል እና የተቋሙ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኢንስፔክተር እታገኝ ዜና በበኩሏ “ተመስገን ዳናን ስንመርጥ ደስ ብሎን ነው። እንደ ክለብ ታዳጊዎች ላይ ለመስራት ፍላጎት ስላለን እና ክለቡን በሚገባ ስለሚያውቅ ወደተሻለ ተፎካካሪነት ያመጣናል ብለን እናምናለን። ላሰብነው ዕቅድ እሱን አሰልጣኝ በማድረጋችን ዕድለኛ ነን” በማለት ሀሳቧን ገልጻለች፡፡

አዲሱ የክለቡ አሰልጣኝ በመሆን በይፋ የተሾመው ተመስገን ዳና በበኩሉ “ደቡብ ፖሊስ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ብዙ አበርክቷል። እግርኳሱን ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱን ስፖርት ትልቅ ደረጃ ለማድረስ እየሰራ ያለ ነው። ይሄ ቡድን ወጣቶች ላይ የሚሰራ በመሆኑ ሌሎች ክለቦች ላይ የመስራት ዕድል እያለኝ ነው ደቡብ ፖሊስን የመረጥኩት። በተጨማሪም ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻለ ተፎካካሪ ለማድረግ ነው ዕቅዴ። ክለቡን የማሰልጠን ዕድልን በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ። በ2012 ደቡብ ፖሊስ ከዚህ ቀደም ያላሳካቸውን ስኬቶች አሳካለው የሚል ትልቅ እምነት አለኝ። ” ብሏል።

በመቀጠል በስፍራው ከተገኙ ጋዜጠኞች ጥያቄ ከተነሳ በኋላ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

አሰልጣኝ ተመስገን ዳና

ለፕሪምየር ሊጉ አዲስ መሆኑ

“በእርግጥ ለፕሪምየር ሊጉ አዲስ አሰልጣኝ ነኝ። አዲስ ነኝ ማለት ግን ለእግር ኳሱ አዲስ ነኝ ማለት አይደለም። በደንብ አድርጌ የኢትዮጵያን እግር ኳስ አውቀዋለሁ። ለ20 ዓመታት ተመልክቼዋለሁ፤ ለአንድ ዓመት ደግሞ ውስጡ ገብቼ ሰርቼበታለሁ። ከዛ ውጪ ስልጠናው ለኔ አዲስ አይደለም። ውድድሩም ለኔ አዲስ ይሆናል የሚል እምነት የለኝም። ወጣት አሰልጣኝ እንደመሆኔ ከወጣቶች ጋር ተባብሮ በመስራት ቡድኑን ወደተሻለ ደረጃ ማምጣት ይቻላል የሚል እምነት አለኝ። ስለዚህ ስጋት ይኖራል ብዬ አላምንም”

አቶ ታሪኩ ኡጋሞ

ክለቡ ከዐምናው ምን ተምሯል? ወደ ፕሪምየር ሊግ እንደመመለሱ ከአሁኑ ምን ታስቧል?

“ዐምና በነበረው ሂደት ደቡብ ፖሊስ ዝቅተኛ ውጤት ነበረው። አሁን ግን የነበሩትን ስህተቶች በማረም ጠንከር ያለ ተወዳዳሪ ለመሆን እንሰራለን። ባለኝ መጠነኛ ልምድ እንዳየሁት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብዙም የተራራቀ አይደለም፤ የተቀራረበ ነው። በጥቃቅን ስህተቶች አንዱ ክለብ ይሸነፋል አንዱ ደግሞ ያሸንፋል። እውነት ነው እኛጋ ትናንሽ ስህተቶች ነበሩ፤ እነሱን አሁን በሚገባ እንቀርፋለን። አሰልጣኙም በዚህ በኩል ዝግጅት እያደረገ ነው። ካለፈው ዓመት ተምረን ጥሩ ቡድን ለመገንባት በዝግጅት ላይ ነን።

” በስፖርታዊ ጨዋነት ላይም የክለቡ ተጫዋቾችም ሆኑ መላው የክለቡ ቤተሰብን ለማስተማር ተዘጋጅተናል። ፌዴሬሽኑ ያወጣውን የደመወዝ ጣሪያ ስርዓት ተከትለን አዝናኝ እና ማራኪ እግር ኳስን የሚያሳይ እንዲሁም ወጣቶችን የሚያበቃ ቡድን ለመገንባት ቆርጠን ተነስተናል።”

የክለቡ ስራአስኪያጅ በመጨረሻ ንግግራቸው ለአሰልጣኙ ሙሉውን ኃላፊነት እና ነፃነት የሰጡ መሆናቸውን የገለፁ ሲሆን በአሰልጣኙም ምርጫ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት የማዋቀር መብት መሰጠቱን ገልፀዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ