ሴካፋ U20 | የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ዩጋንዳ አመራ

ከነሀሴ 27 ጀምሮ በአዳማ ከተማ ዝግጅቱን ሲያደርግ የቆየው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ላይ ለመካፈል 26 የልዑካን አባላትን በመያዝ ወደ ዩጋንዳ አምርቷል፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ የምስራቅ አፍሪካን የእግር ኳስ ደረጃ ከፍ ያደርጋል የተባለለት ይህ የታዳጊዎች ውድድር ነገ በአስተናጋጇ ከተማ ካምፓላ ይጀመራል፡፡ በአሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ እየተመራ በአዳማ ዝግጅት ሲያደርግ የነበረው ቡድኑ በመጀመሪያው ዙር 28 ተጫዋቾችን የጠራ ሲሆን አራቱ ተጫዋቾች ለውድድሩ ዕድሜያቸው አልደረሰም በሚል በተጠባባቂነት በተያዙ አራት ተጫዋቾች ተተክተው ዝግጅታቸውን ቀጥለዋል፡፡

ቡድኑ በዝግጅት ወቅት የትጥቅ እና የክትትል ችግር እንደነበረ የገለፁ ሲሆን ዛሬ ግን ፌዴሬሽኑ በመጠኑም ቢሆን ችግራቸውን ቀርፎላቸው 20 ተጫዋቾች፣ ሦስት የአሰልጣኝ ቡድን አባላት እና የፌድሬሽኑን ተወካይ ጨምሮ በድምሩ 26 የልዑክ አባላትን በመያዝ ወደ ስፍራው ተጉዘዋል፡፡

አሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ መሐመድ አበራ (አጥቂ)፣ አዲሱ ተስፋዬ (ተከላካይ)፣ ሚኪያስ ታምራት (አማካይ) ከማይጓዙት መካከል መሆናቸውን ሲገልፁ የሀዋሳ ከተማው አጥቂ መስፍን ታፈሰ ለዋናው ብሔራዊ ቡድን በመመረጡ ከዕሁዱ የቻን ማጣሪያ ጨዋታ በኃላ ወደ ስፍራው ተጉዞ ለሁለተኛው የምድብ ጨዋታ እንደሚደርስ ገልፀዋል።

የተጓዙት 20 ተጫዋቾች ስም ዝርዝር

ግብ ጠባቂዎች (3) አቡሽ አበበ (ወላይታ ድቻ)፣ ተመስገን ዮሀንስ (ቅ/ጊዮርጊስ)፣ ምንተስኖት ጊምቦ (ሀዋሳ ከተማ)

ተከላካዮች (9) አዛርያስ አቤል (ወላይታ ድቻ)፣ ሀብታሙ ኃይሌ (መከላከያ)፣ ፉአድ ነስሩ (ኢ/ቡና)፣ ያብስራ ሙሉጌታ (ቅ/ጊዮርጊስ)፣ ፀጋአብ ዮሀንስ (ሀዋሳ ከተማ)፣ አቡበከር ሙራድ (ቅ/ጊዮርጊስ)፣ ቃልአብ ፍቅሩ (ኢ/ቡና)፣ መስፍን ጳውሎስ (መከላከያ)፣ እዮብ ማቲዮስ (መከላከያ)

አማካዮች (5) ሙሴ አበለ (ኢ/ቡና)፣ ብሩክ መንገሻ (አዳማ ከተማ)፣ አድናን ረሻድ (አምቦ ጎል)፣ ዊሊያም ሰለሞን (መከላከያ)፣ አበባየው አጪሶ (ወላይታ ድቻ)

አጥቂዎች (3) ሀብታሙ መኮንን (ሀዋሳ ከተማ)፣ አቤል ነጋሽ (መከላከያ)፣ ታምራት ስላስ (ወላይታ ድቻ)

ከምድብ ሁለት የተደለደለችው ኢትዮጵያ ዕሁድ 10:00 የመጀመሪያ ጨዋታዋን ከታንዛኒያ የምታደርግ ይሆናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ