በፊፋ ጥሪ የቀረበላቸው አሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ እና መኮንን ኩሩ ወደ ጣሊያን አምርተዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ እና የቴክኒክ ዳይሬክተሩ መኮንን ኩሩ በፊፋ የዓለም ምርጥ ተጫዋቾች ምርጫ ላይ ለመታደም ወደ ጣልያን ትላንት ምሽት አምርተዋል፡፡

የፊፋ የዓለም ምርጥ ተጫዋች ምርጫ የፊታችን ሰኞ በጣሊያኗ ሚላን ከተማ የሚከናወን ሲሆን በዚህ ምርጫ ላይ ከዓለም ሀገራት የተወጣጡ በርካታ የእግር ኳስ ሰዎች ተገኝተው የሚታደሙ ይሆናል፡፡ ፊፋም በዚህ መድረክ ላይ ሁለት ባለሙያዎች ከኢትዮጵያ በእለቱ እንዲገኙ ባቀረበው ግብዣ መሠረት የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ መኮንን ኩሩ ትላንት ምሽት ወደ ስፍራው አቅንተዋል፡፡

ሰኞ ከሚደረገው የፊፋ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋቾች ምርጫ ባለፈ ቅዳሜ (ዛሬ) የ2019 የሴቶች የዓለም ዋንጫ ግምገማ ላይም አሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ የምትገኝ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ