ነቀምቴ ከተማ በቅርቡ ህይወቱ ላለፈው ተጫዋች ቤተሰቦች ድጋፍ አደረገ

ባለፈው የውድድር ዓመት በነቀምቴ ከተማ ሲጫወት የነበረውና በአንድ ምሽት በተተኮሰ ጥይት ህይወቱ ላለፈው ወንድወሰን ዮሐንስ ቤተሰቦች የነቀምቴ ከተማ ክለብ የገንዘብ ድጋፍን አበርክቷል።

ባሳለፍነው የ2011 የውድድር ዘመን ግንቦት ወር መጨረሻ ላይ በነቀምቴ ከተማ በአማካይ ስፍራ ሲጫወት የነበረው ወንድወሰን ዮሐንስ የክለቡ ተጫዋቾች ምሽት ላይ ከሆቴል እራት ተመግበው ሲወጡ በአካባቢው በተፈጠረ ግርግር በተተኮሰ ጥይት በ27 ዓመቱ ህይወቱ ማለፉ ይታወሳል፡፡

ተጫዋቹ በህይወት በነበረበት ወቅት እናት እና አባቱ በህይወት ያለመኖራቸውን ተከትሎ ታናሽ ወንድም እና እህቶቹን የሚያስተዳድር መሆኑ የተጫዋቹን አሟሟት ይበልጥ አሳዛኝ አድርጎታል። ይህን የተመለከቱ ወጣቶችም ኮሚቴ በማቋቋም ለቤተሰቡ ዘላቂ ኑሮ በማሰብ የድጋፍ ማሰባሰብ ሥራን የሰሩ ሲሆን በርካታ የሀገራችን ክለቦች ይህን ሀሳብ በመደገፍ ለቤተሰቡ በክለቦቻቸው ስም ከፍተኛ አስተዋጽኦን አድርገዋል። በተለይ የወንድወሰን ቤተሰቦች እጅግ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ እና የራሳቸውን መኖሪያ ቤት እንኳን የሌላቸው በመሆኑ ተጫዋቹ የተወለደበት ሀዋሳ ኮረም ሰፈር ነዋሪዎች ከምስራቅ ክፍለ ከተማ ጋር በመተባበር እጅግ ዘመናዊ በሚባል መልኩ ቤት አሰርቶ የሰጣቸው ከመሆኑም ባለፈ መተዳደሪያ እንዲሆናቸው የባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪም አበርክቶላቸዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ የጤና ቡድኖች ውድድር በማድረግ ለዚህ ቅዱስ አላማ የራሳቸውን ድጋፍ ማበርከት የቻሉ ሲሆን ትላንት ደግሞ የነቀምት ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ለተጫዋቹ ቤተሰቦች በክለቡ ስም ድጋፍን አድርገዋል፡፡ በዕለቱ የነቀምቴ ከተማ ዋና አሰልጣኝን ጨምሮ የተጫዋቹ ቤተሰቦች በተገኙበት ከተጫዋቾች የ70 ሺህ ብር ከክለቡ ደግሞ 70 ሺህ ብር በድምሩ ከ140 ሺህ ብር በላይ በመኖሪያ ቤት ተገኝተው ሰጥተዋል፡፡

አቶ ኬኔሳ አመንቴ የነቀምቴ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ቦርድ አባል በእለቱ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ “ጉዳዩን ሁሉም ያውቀዋል፣፤ የተፈጠረው ድንገት በመጣ እና ከምንም ጋር የማይገናኝ ክስተት ነበር። በጣም ትልቅ ሀዘን ተሰምቶናል። በጣም ጨዋ ልጅ ነበር። ከቡድኑ አሰልጣኞች ጋርም ከተጫዋቾቹ ጋርም ከማንኛውም ጋር የነበረው ግንኙነት ጥሩ የነበረና ስነምግባር ያለው የምንኮራበት ልጅ ነበር። የሆነ ሆኖ ህይወቱ በዚህ መንገድ አልፏል፡፡ ከክስተቱ በኋላ ኮሚቴ አዋቅረን ወደዚህ መጥተናል። ይህን ከኛም ሆነ ከነቀምቴ እግር ኳስ ወዳድ ህዝብ ከልብ የማይወጣና የማይዘነጋ ነው። አሁን በአካል መጥተን ከቤተሰቦቹ ጋር ሆነን ሀዋሳ ከተማ የተደረገውን ነገር ስናይ በጣም ደስ ብሎናል።

” በቀጣይ የወንድወሰን ቤተሰብ ውስጥ የመማር ፍላጎት ያለው ካለ ለማስተማር ዝግጁ ነን። ወለጋ ዩኒቨርሲቲ እና ሀዋሳም ቢሆን እንዲማሩ እናደርጋለን። ዛሬ ወንዴ ባይኖርም ነቀምቴ ወደ ፕሪምየር ሊግ አድጓል። የሱ ልፋት እና ጥረት እዚህ ውስጥ አለበት። አሁን የነቀምቴ ቡድን ከፍተኛ መነቃቃት ውስጥ ነው። ምርጥ ሦስተኛ ሆኖም ቢሆን ወደ ፕሪምየር ሊግ ገብቷል። ይሄ በዕድል ወይም በዕጣ የመጣ አይደለም። በተጫዋቾቹ እና በወንዴ ጥረት የመጣ ነው። ነቀምቴ ሲያድግ የወንዴ ስምም ያድጋል፤ አንዱ የክለቡ ታሪክም ሆኖ ይቀጥላል። ያደረግነው ድጋፍ በቂ ነው አንልም፤ ይህ ድጋፋችንም ይቀጥላል። ሁሌም ከጎን አለን።”

በመጨረሻም እንደ ቦርድ አባሉ አቶ ኬኔሳ ገለፃ ከሆነ ክለቡ በዘንድሮ የ2012 ዓመት ጠንካራ ቡድን ሆኖ ለመቅረብ ደጋፊውን በማስተባበር እንደሚሰሩ እና የነቀምቴ ህዝብም የወንደሰንን አላማ ለማሳካት ከክለቡ ጎን እንደሚቆም ገልጸዋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ