ደደቢቶች የአራት ተጫዋቾች ዝውውር አጠናቀቁ

አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊትን የቀጠሩት ደደቢቶች የዳንኤል አድሐኖም፣ ሃፍቶም ቢሰጠኝ፣ ክብሮም ግርማይ፣ እና ክፍሎም ሐጎስን ዝውውር አጠናቀዋል።

የክለቡ የመጀመሪያ ፈራሚ የቀኝ መስመር ተከላካዩ ዳንኤል አድሐኖም ነው። ከዚህ ቀደም ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ መቐለ 70 እንደርታ እና ወልዋሎ የተጫወተው ዳንኤል ከአሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት ጋር በድጋሚ የሚገናኝ ይሆናል።

ሁለተኛው የክለቡ ፈራሚ ግብጠባቂው ሃፍቶም ቢሰጠኝ ነው። ላለፈው አንድ ዓመት ከስድስት ወር በስሑል ሽረ ጋር ቆይታ የነበረው ይህ የቀድሞ የሃዋሳ ከተማ፣ መቐለ 70 እንደርታ፣ ወልዋሎ እና አዲስ አበባ ከተማ ግብ ጠባቂ ለቋሚነት ከሙሴ ዮሐንስ ጋር ይፎካከራል።

ሦስተኛው የቡድኑ ፈራሚ አማካዩ ክብሮም ግርማይ ነው። ከዚህ ቀደም ለመቐለ 70 እንደርታ፣ አውስኮድ፣ ወልዋሎ እና ወሎ ኮምቦልቻ የተጫወተው ይህ ተጫዋች ባለፈው የውድድር ዓመት ከአክሱም ከተማ ጋር ቆይታ ማድረጉ ሲታወስ ከአሰልጣኙ ጋርም በድጋሚ ይገናኛል።

አራተኛው ደደቢት ፈራሚ ክፍሎም ሐጎስ ነው። ክፍሎም ለፋሲል ከነማ እና ድሬዳዋ ከተማ ከዚህ በፊት መጫወት ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ