አርባምንጭ ከተማ ሁለት ተጫዋቾችን አስፈረመ

የዝውውር መስኮቱን ዘግየት ብለው የተቀላቀሉት አርባምንጭ ከተማዎች አማካዩ ምንተስኖት አበራ እና ሁለገቡ የመስመር ተጫዋች አድማሱ ጌትነትን አስፈርመዋል።

የቀድሞው የአርባምንጭ ከተማ አማካይ ምንተስኖት አበራ ቡድኑ በፕሪምየር ሊግ ተካፋይ በነበረባቸው መጨረሻ ሦስት ዓመታት በተለይ ከአማኑኤል ጎበና ጋር ጥሩ የመሀል ሜዳ ጥምረት በመፍጠር ለቡድኑ ከፍተኛ ግልጋሎት መስጠቱ ይታወሳል። አርባምንጭን ለቆ በ2011 የውድድር ዘመን ወደ ሀዋሳ ከተማ በማምራት ካሳለፈ በኋላም ወደ ቀድሞ ክለቡ ተመልሷል።

ሌላኛው የክለቡ ፈራሚ በቀኝም ሆነ በግራ የመስመር አማካይነት መጫወት የሚችለው ሁለገቡ የመስመር ተጫዋች አድማሱ ጌነትነት ነው። የቀድሞው የቡራዩ፣ ሱሉልታ ከተማ እና ካፋ ቡና ተጫዋቾች አድማሱ የአሰልጣኝ መሳይ ተፋሪን የመስመር ተጫዋቾች አማራጭ ያሰፋል ተብሎ የሚጠበቅ ተስፈኛ ተጫዋች ነው፡፡

በተያያዘ ዜና የክለቡ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ስንታየሁ ንጎሴ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ክለቡ ከዚህ ቀደም በደረሰው ደብዳቤው መሠረት አሁን ድረስ ራሳቸውን በፕሪምየር ሊጉ ጥሩ ተፎካካሪ አድርገው ለመቅረብ እየሰሩ እንደሚገኙ ገልፀዋል። (ፌዴሬሽኑ በትላንትናው ዕለት በላከው ደብዳቤ ክለቡ በከፍተኛ ሊጉ እንደሚቀጥል መግለፁ ይታወቃል።)


© ሶከር ኢትዮጵያ