ወልዋሎ የአንድ ወጣት ተጫዋች ዝውውር ሲያጠናቀቅ ከምክትል አሰልጣኙ ጋር ተለያይቷል

በዝውውር መስኮቱ በስፋት እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት ወልዋሎዎች በአጥቂ ቦታ ላይ የሚሰለፈው ወጣቱ አጥቂ ብሩክ ሰሙን ሲያስፈርሙ ከምክትሉ ሀፍቶም ኪሮስ ጋር ተለያይተዋል።

በርካታ ውጤታማ ወጣት ተጫዋቾች ባፈራው ሐረር ሲቲ እና ባለፈው ዓመት ደግሞ የ20 ዓመት ፕሪምየር ሊግ ምድብ ሀ አሸናፊ በነበረው አዲስ አበባ ከተማ ጥሩ ውጤት ላይ የጎላ ድርሻ የነበረው ወጣቱ አጥቂ ብሩክ ሰሙ ቀደም ብሎ ከቢጫ ለባሾቹ ጋር ልምምድ ሲጀምር በትናንትው ዕለትም በይፋ የክለቡ ተጫዋች ሆኗል። ተጫዋቹ በመስመር እና መሐል አጥቂነት መጫወት የሚችል ሲሆን በወጣቶች ለተገነባው ወልዋሎም ጥሩ ግብዓት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

በሌላ ዜና ባለፉት ዓመታት ከወልዋሎ ጋር ቆይታ የነበረው ወጣቱ አሰልጣኝ ሀፍቶም ኪሮስ ከቡድኑ ጋር ተለያይቷል። በቡድኑ የተለያዩ አሰልጣኞች ስር ረዳት ሆኖ የሰራው ወጣቱ አሰልጣኝ በ2008 ከአሰልጣኝ እንድርያስ ብርሃኑ፣ በ2010 ከአሰልጣኝ ብርሃኔ ገብረእግዚአብሔር መለያየት በኋላ ቡድኑን በጊዚያዊነት በዋና አሰልጣኝ መምራቱ ሲታወስ ሥሙም ከአንድ የብሄራዊ ሊግ ቡድን እየተያያዘ ይገኛል።


© ሶከር ኢትዮጵያ