ድሬዳዋ ከተማ ፋሲል አስማማውን አስፈርሟል

የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቹ ፋሲል አስማማው ከፋሲል ከነማ ጋር በስምምነት በመለያየት ወደ ወደ ምስራቁ ክለብ አምርቷል፡፡

በቢሾፍቱ የቅድመ ውድድር ጊዜ ዝግጅታቸውን ከጀመሩ ሳምንታት ያስቆጠሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በርካታ አዳዲስ እና ነባር ተጫዋቾችን በጋራ በመያዝ ዝግጅታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ክለቡ እስከ አሁን ስምንት አዳዲስ ተጫዋቾችን ያስፈረመ ሲሆን አሁን ደግሞ ዘጠነኛ ተጫዋች በማድረግ አጥቂው ፋሲል አስማማውን ወደ ስብስቡ አካቷል፡፡ አዲሱ የድሬዳዋ ፈራሚ በ2010 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በለገጣፎ ለገዳዲ በፊት አጥቂነት ተሰልፎ በመጫወት አስር ግቦችን አስቆጥሮ አምና ፋሲል ከነማን በሁለት ዓመት ውል መቀላቀሉ ይታወሳል፡፡ ሆኖም ተጫዋቹ በዐፄዎቹ ቤት ቆይታው በጉዳት ምክንያት ለበርካታ ጊዜያት መጫወት ባይችልም በዓመቱ መጨረሻ ላይ በማገገም የመሰለፍ ዕድልን ሲያገኝ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በፋሲል ቀሪ የአንድ ዓመት ኮንትራት የነበረው ይህ አጥቂ አሁን ደግሞ ከአፄዎቹ ጋር በስምምነት በመለያየት ወደ ድሬዳዋ ከተማ ማምራቱ ታውቋል፡፡

ከድሬዳዋ ፖሊስ እና ከናሽናል ሲሚንት ለተጫዋቾች የሙከራ ዕድልን እየሰጡ የሚገኙት ብርቱካናማዎቹ ከሀገር ውስጥ ተጫዋቾች ባለፈ ለውጪ ሀገር ተጫዋቾችም የሙከራ ዕድልን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ