ፋሲል ከነማ ለተጫዋቾች የሙከራ ዕድል እየሰጠ ይገኛል

በአዲሱ አሰልጣኙ ሥዩም ከበደ እየተመራ በባህር ዳር ቅድመ ዝግጅቱን እያደረገ የሚገኘው ፋሲል ከነማ ከተስፋ ቡድኑ ያመጣቸውና ኮንትራት የጨረሱትን ጨምሮ ሌሎች ተጫዋቾችን ለመመልከት የወዳጅነት ጨዋታ አድርጓል።

በባህር ዳር ከተማ የሚገኘው ኢትዮጵያ-ተስፋ ወጣት ቡድን (የያሬድ ልጆች) በመባል የሚጠራው ቡድን ጋር ትላንት ጨዋታ ያደረገው ፋሲል ከነማ ከእረፍት በኋላ ከተስፋ ቡድኑ ያደጉ እና ሌሎች ወጣቶችን በማስገባት ለማየት የተሞከረ ሲሆን አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ በአብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ደስተኛ እንደሆኑና በቀጣይም እድል እንደሚሰጣቸው ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል። ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንም ጋር የወዳጅነት ለመድረግ እቅድ እንዳለቸው የገለፁልን አሰልጣኙ ቡድኑን ይበልጥ ለማጠናከር ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙም ገልፀውልናል።

በክለቡ በቢጫ ታሴራ ሲጫወት የቆየው ዳንኤል ዘመዴ ኮንትራቱን የጨረሰ ቢሆንም በስብስቡ ውስጥ ተካቶ ሙከራ ለማድረግ ወደ ባህር ዳር የተጓዘ ሲሆን በወዳጅነት ጨዋታው ላይም ተስፋ ሰጪ ብቃቱን አሳይቷል። በተጨማሪም የሽዋስ በለው ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበል እና ግቦችን በማስቆጠር በጨዋታው ላይ ጎልቶ መታየት ሲችል ሌላኛው ተስፈኛ ታዳጊ ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ እና የመስመር ተከላካዩ ሄኖክ ይትባረክ ሌሎች ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ካሳዩት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

በአጠቃላይ ፋሲል ከነማ ለዘንድሮው የውድድር ዓመት 4 ተጫዋቾችን ከተስፋ ቡድኑ (ክብረት ካሳሁን፣ ናትናኤል ማስረሻ፣ ኤፍሬም ኃይሉ፣ ሄኖክ ይትባረክ) እንዲሁም ወደ ዋናው ቡድን አድገው ኮንትራት የጨረሱት ያሬድ አበበ እና ዳንኤል ዘመዴን በተጨማሪም የጎንደር ዩኒቨርስቲ የሲቪል ምህንድስና ምሩቅ ኤፍሬም ክፍሌን የሙከራ ዕድል በመስጠት ዝግጅት እያደረጉ ሲገኙ አሰልጣኙን ያሳመኑት ተጫዋቾች የዋናው ቡድን አካል እንደሚሆኑ ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ