የዩጋንዳ ብሄራዊ ቡድን ባህር ዳር ገብቷል

የፊታችን እሁድ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታ የሚያደርጉት ዩጋንዳዎች ከሰዓታት በፊት ባህር ዳር ገብተዋል።

ከሳምንት በፊት ሴባስትያን ዴሳብርን በመተካት አሰልጣኝ በሆኑት ጆናታን ሚክንስትሪ የሚመሩት ዩጋንዳዎች ከቡሩንዲ ብሄራዊ ቡድን ጋር ላለባቸው የቻን የሁለተኛ ዙር የማጣሪያ ጨዋታ ዝግጅታቸውን ባህር ዳር ላይ ነገ ይጀምራሉ። ወጣቱ ሰሜን አይርላንዳዊ አሰልጣኝ ጆናታን ሚክንስትሪ ጥሪ ያደረጉላቸው 21 ተጨዋቾችን አዲስ አበባ ላይ እንዲሰባሰቡ አድርገው ልዑካኑን በመምራት ከሰዓታት በፊት ወደ ባህር ዳር አምርተዋል።

አዲስ አበባ የተሰባሰቡት 21 ተጨዋቾችን እና ከካምፓላ የተነሳውን የአሰልጣኞች ቡድን ስብስብን ጨምሮ ወደ ባህር ዳር የገባው ልዑካን ማረፊያውን በዊን ሆቴል እንዳደረገ ለማወቅ ተችሏል። ቡድኑ ነገ እና ከነገ በስትያ በባህር ዳር ትንሿ ሜዳ እና ዋናው ሜዳ ልምምድ ካከናወነ በኋላ የፊታችን እሁድ በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን በወዳጅነት ጨዋታ ይገጥማል።


© ሶከር ኢትዮጵያ