አዳማ ከተማ ተስፋዬ ነጋሽ አስፈርሟል

አዳማ ከተማ የቀድሞውን የክለቡ ሁለገብ ተጫዋች ተስፋዬ ነጋሽን አስፈረመ፡፡

በተለያዩ የአጥቂ ሚናዎች እና በመስመር የሚጫወተው ተስፋዬ ነጋሽ ከዚህ ቀደም በጥቁር ዓባይ፣ ዳሽን ቢራ እና ወልዲያ የተጫወተ ሲሆን ለአዳማ ከተማ ለሦስት ዓመታት ተጫውቶ በ2011 የውድድር ዓመት ወደ ቀድሞ ክለቡ ወልዲያ ተመልሶ ዓመቱን አሳልፏል። ከአንድ የውድድር ዘመን በኋላም በድጋሚ ተመልሶ አዳማ ከተማን መቀላቀል ችሏል።

የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን በአዳማ ከተማ እየሰሩ የሚገኙት አዳማ ከተማዎች ቀደም ብለው ወደ ዝውውሩ በመግባት በርካታ ተጫዋቾችን አስፈርመው የነበሩ ቢሆንም በአዲሱ የክፍያ ደንብ መሠረት አምስት አዳዲስ ፈራሚዎችን ለመልቀቅ ተገዷል፡፡ ከሰሞኑም በምትኩ አዳዲስ ልጆችን እየቀላቀለ የሚገኘው ክለቡ ተስፋዬን ጨምሮ በክለቡ የተጫወቱት ሚካኤል ጆርጅ እና የኋላሸት ፍቃዱን ወደ ክለቡ መልሷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ