ወላይታ ድቻ የዘላለም ኢያሱን ውል ሲያራዝም ለሁለት ተጫዋቾች የሙከራ ዕድልን ሰጥቷል

በቦዲቲ የቅድመ ውድድር ዘመን ዝግጅት እያደረገ የሚገኘው ወላይታ ድቻ የሁለገብ ተጫዋቹ ዘላለም ኢያሱን ውል ሲያራዝም ለሁለት ተጫዋቾች የሙከራ ጊዜን ሰጥቷል፡፡

ከክለቡ የታዳጊ ቡድን በማደግ ያለፉትን ሦስት ዓመታት ያሳለፈው የመስመር እና የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ዘላለም ኢያሱ በክለቡ ለተጨማሪ ዓመት የሚያቆየውን ውል ፈርሟል፡፡ ተጫዋቹ አምና በጉዳት ምክንያት ከሜዳ ርቆ የቆየ ሲሆን አሁን ወደ ጤንነቱ መመለሱ ታውቋል።

ክለቡ በተጨማሪም ለሁለት ተጫዋቾች የሙከራ ዕድልን የሰጠ ሲሆን የቀድሞው የቡድኑ አማካይ አሸናፊ ሽብሩ ዕድሉን ካገኙት ውስጥ ነው። ድቻን ከለቀቀ በኋላ በኢትዮ-ኤሌክትሪክ እና ጅማ አባጅፋር መጫወት የቻለው አሸናፊ ከጉዳቱ ካገገመ በኋላ በሀዋሳ ከተማ ልምምድ ሲሰራ ቆይቷል።

ሌላኛው የሙከራ ዕድል ያገኘው አጥቂው ቅዱስ ታደሰ ከመከላከያ ተስፋ ቡድን የተገኘ እና በዲላ ከተማ መጫወት የቻለ ሲሆን በቆይታው አሰልጣኙን ማሳመን ከቻለ ክለቡን የሚቀላቀል ይሆናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ