ሎዛ አበራ ጎል ማስቆጠሯን ቀጥላለች

ዛሬ በተከናወነው የሁለተኛ ሳምንት የማልታ ሴቶች ሊግ ቢርኪርካራ ተጋጣሚውን ሲያሸንፍ ሎዛ አበራ ሁለት ግቦች አስቆጥራለች።

ለማልታው ቢርኪርካራ በመፈረም ባለፈው ሳምንት በመጀመርያ ጨዋታዋ ለክለቡ ሁለት ግቦች አስቆጥራ አንድ ለግብ የሚሆን ኳስ በማመቻቸት ጥሩ አጀማመር ያደረገችው ሎዛ አበራ ዛሬ በተደረገ ጨዋታም ሁለት ግቦች አስቆጥራለች። ቢርኪርካራዎች ተጋጣሚያቸው ኪርኮፕ ዩናይትድን 7-1 ሲያሸንፉ ኢትዮጵያዊቷ አጥቂ በ15ኛው እና 40ኛው ደቂቃዎች ላይ ጎሎችን አስቆጥራለች።

ቀሪዎቹን ቢርኪርካራ ጎሎች ቬሮኒካ ሚስፉድ፣ ቲሬሲ ቱማ፣ ማርያ ሰይድ፣ የሌንያ ካራቦት እና ኬሊ ዊልስ ሲያስቆጥሩ ለባለሜዳዎቹ ኢስቤሌ ማዚቴሊ ብቸኛዋን ጎል አስቆጥራለች።

በአሰልጣኝ ሜላንያ ባያዳ የሚመሩት ቢርኪርካራዎች በቀጣይ ሰኞ በሦስተኛ ሳምንት መርሐ ግብር ምጋግ የተባለ ቡድንን ይገጥማሉ።


© ሶከር ኢትዮጵያ