ወላይታ ድቻ ሁለት ረዳት አሰልጣኞችን ሾመ

ወላይታ ድቻ የአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ረዳት አሰልጣኝ በማድረግ የቀድሞ የክለቡ ተጫዋቾች ግዛቸው ጌታቸው እና ዘላለም ማቲዮስን ሾሟል፡፡

ክለቡ ዐምና የአሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ እና አሸናፊ በቀለ ረዳት የነበረውን ደለለኝ ደቻታን አሁንም ባለበት እንዲቀጥል በማድረግ የአሰልጣኝ ቡድኑን ለማስፋት በማሰብ ነው ተጨማሪ አሰልጣኞችን የሾመው፡፡

ወላይታ ድቻ በ2005 ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሲያድግ የቡድኑ አምበል የነበረው ግዛቸው ጌታቸው የገብረክርስቶስ ቢራራ ረዳት ሆኖ ተሹሟል፡፡ አሰልጣኙ በክለቡ እስከ 2008 አጋማሽ ድረስ በተጫዋችነት ካገለገለ በኋላ እግርኳስን በማቆም ወደ አሰልጣኝነቱ የገባ ሲሆን በ2010 የውድድር ዘመን የመጀመሪያ ዙር ከአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ጋር በዋናው ቡድን እንዲሰራ በረዳትነት ቢሾምም በውጤት መጥፋት ከዋናው ቡድን በመነሳት በወጣት ቡድኑ አሰልጣኝነት ሲሰራ ቆይቷል፡፡ አሰልጣኝ ግዛቸው የክለቡ ከ20 ዓመት በታች ቡድን የዕድሜ ዕርከኑ ቻምፒዮን ሲሆን ቡድኑን የመራ ሲሆን ባስመዘገበው ውጤት መነሻነትም ለዋናው ቡድን ረዳትነት በድጋሚ ተሹሟል፡፡

የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ በመሆን የተሾመው ዘላለም ማቲዮስ ነው፡፡ በተጫዋችነት ዘመኑ ለሀዋሳ ከተማ፣ ሀላባ ከተማ እና ወላይታ ድቻ መጫወት የቻለው ዘላለም እግርኳስን ካቆመ በኋላ በተለያዩ ፕሮጀቶች እና በወላይታ የሴቶች ክለብ ውስጥ አሰልጥኗል። ባለፉት ዓመታት ደግሞ በወላይታ ድቻ ወጣት እና ታዳጊ ቡድኖች ውስጥ በግብ ጠባቂ አሰልጣኝነቱ ሰርቷል፡፡ በቅርቡ በሴካፋ የተወዳደረው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ነበረው ዘላለም አሁን ደግሞ በወላይታ ድቻ ዋናው ቡድን የሚሰራ ይሆናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ