ሀዋሳ ከተማ ሁለት ተጫዋቾችን አስፈረመ

ሀይቆቹ በዛሬው ዕለት ካሜሩናዊው ግብ ጠባቂ ቢሊንጌ ኢኖህ እና የቀድሞው የክለቡ የተስፋ ቡድን ተጫዋች የነበረው ወጣቱ አማካይ አቤኔዘር ዮሐንስን አስፈርመዋል፡፡

ቢሊንጌ ኢኖሆየህ ለሀገሩ ክለቦቸ ሮምዴ አድጃ እና አቺሊ ለተባሉ ክለቦች የተጫወተ ሲሆን ከስምንት ዓመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ በኃላ ረጅም ዓመታት በሀገራችን የተለያዩ ክለቦች በመጫወት አሳልፏል፡፡ በሐረር ቢራ፣ ውሀ ስራዎች፣ መቐለ 70 እንደርታ እና ወልዲያ የተጫወተው ግብ ጠባቂው በተለይም በወልዲያ ቆይታው ድሬዳዋ ላይ በፕሪምየር ሊጉ ከግብ ክልሉ በመለጋት ግብ ማስቆጠሩም ይታወሳል፡፡ ባለፈው የውድድር ዓመት ወደ ወልቂጤ ከተማ አምርቶ ቡድኑ ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲያድግ አስተዋጽኦ ካበረከተ በኋላ የዘንድሮ ማረፊያውን ሀዋሳ ከተማ አድርጓል፡፡

ሌላኛው ክለቡን የተቀላቀለው የአማካይ ስፍራ ተጫዋች የሆነው ወጣቱ አቤኔዘር ዮሐንስ ነው፡፡ በሀዋሳ ከተማ የተስፋ ቡድን ከ2008 እስከ 2009 ከቆየ በኋላ በ2010 በትምህርት ጉዳይ መጫወት ባይችልም ከዐምና ጀምሮ ከክለቡ ጋር ልምምድ ሲሰራ ከቆየ በኋላ ለዘንድሮው የውድድር ዘመን ፊርማውን አኑሯል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ