ፋሲል ከነማ ወጣት ተጫዋች አስፈረመ

ዐፄዎቹ የሙከራ እድል በመስጠት ሲመለከቱት የቆዩት ኤፍሬም ክፍሌን ሲያስፈርሙ ሌላው ወጣት ዳንኤል ዘመዴን ውል አድሰዋል።

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሲቪል ምህንድስና ምሩቅ የሆነው ኤፍሬም ክፍሌ ጎንደር ከተማ ላይ ሲደረጉ በነበሩ የውስጥ ውድድሮች ላይ ኮኮብ ተጫዋች እና ኮኮብ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ያጠናቀቀ ሲሆን ጎንደር ዩኒቨርሲቲንም ወክሎ አዳማ ከተማ በተደረገው የመላው የዩኒቨርስቲዎች ውድድር ላይ ተሳትፎ በምድብ ጨዋታዎች ላይ አራት ጎሎችን አስቆጥሯል። በውድድሩ ላይ አሁን በወላይታ ድቻ ከሚገኘው አንተነህ ጉግሳ ጋር አብሮ የተጫወተው ኤፍሬም አሁን ደግሞ በዐፄዎቹ ቤት ከአንተነህ ወንድም ሽመክት ጉግሳ ጋር የሚጫወት ይሆናል።

ጥሩ የኳስ ተሰጥኦ እንዳለው የተረዱት ፋሲሎች የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ በአዲሱ አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ አማካኝነት የሙከራ እድል የሰጡት ሲሆን በቆይታውም አሰልጣኙን በማሳመኑ ለሁለት ዓመታት ሊፈርም ችሏል። ” ጎንደር ከተማ በቆየሁባቸው ዓመታት ህዝቡ ለኔ ጥሩ ነገር ነበርው። ጥሩ ለነበረልኝ ህዝብ ደግሞ ያለኝን ነገር ለመስጠት ዝግጁ ነኝ፤ የመጀመሪያ ክለቤ አፄዎቹ በመሆኑ ትልቅ ኩራት ይሰማኛል።” ሲልም አስተያየቱን ለሶከር ኢትዮጵያ ሰጥቷል።

በተያያዘ ዜና ፋሲል ከነማ የተከላካዩ ዳንኤል ዘመዴን ውል አድሷል። በ2008 የዳሽን ተስፋ ሲፈርስ ወደ ዐፄዎቹ ቤት ያቀናው ታዳጊው ያለፉትን ሁለት ዓመታት በቢጫ ቴሴራ ቡድኑን አገልግሎ አሁን ደግሞ ተጨማሪ ለሁለት ዓመታት የሚያቆየውን ውል ተፈራርሟል።


© ሶከር ኢትዮጵያ