ድሬዳዋ ከተማ ናይጄሪያዊ አጥቂ አስፈረመ

ድሬዳዋ ከተማ ለአንድ ሳምንት በሙከራ ሲመለከታቸው ከነበሩ የውጪ ዜጋ ተጫዋቾች መካከል የናይጄሪያ ዜግነት ያለው ባጆዋ አዴሰገንን አስፈርሟል፡፡

ለበርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ሀገር ተጫዋቾች የሙከራ ዕድልን እየሰጠ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ ተስፋ ሰጪ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ሲያደርጉ የነበሩትን ተጫዋቾች ወደ ክለቡ ስብስብ ኮንትራት በመስጠት እያስፈረመ የሚገኝ ሲሆን አሁን ደግሞ የናይጄሪያ ዜግነት ያለውን የ26 ዓመት አጥቂ ፕሪንስ ባጆዋ አዴሰገንን በአንድ ዓመት ውል አስፈርሟል፡፡ ተጫዋቹ በሀገሩ ክለቦች ኢንጉ ሬንጀርስ እና ሰንሻይን ስታርስ የተጫወተ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣትም ሶስተኛ ክለቡ የሆነውን ድሬዳዋ ከተማን መቀላቀልም ችሏል፡፡

ላይቤሪያዊውን አጥቂ ኢታሙና ኪሙኒን እና ሀብታሙ ወልዴን ያጣው ድሬዳዋ ክፍተቱን ለመሙላት ሪችሞንድ አዶንጎን በቅርቡ ያስፈረመ ሲሆን ፕሪንስ ባጆዋ ሁለተኛ የውጪ ሀገር የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች ሆኗል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ