ከፍተኛ ሊግ | ደደቢት ሁለት ተጫዋቾች አስፈረመ

በዝውውር መስኮቱ በርከት ያሉ ተጫዋቾች ያስፈረሙት ሰማያዊዎቹ ኄኖክ ገብረመድኅን እና ክብሮም አስመላሽን አስፈርመዋል።

ከዚህ ቀደም በደደቢት፣ ዳሽን ቢራ እና መቐለ 70 እንደርታ የተጫወተው ግዙፉ አጥቂ ኄኖክ ቀደም ብሎ ከሰማያዊዎቹ ጋር ልምምድ የጀመረ ሲሆን በዛሬው ዕለት በይፋ ፊርማውን ማኖሩ ተከትሎ ከበርካታ ዓመታት በኃላ ወደ ቀድሞ ክለቡ የሚመለስ ይሆናል። ለዓመታት መቐለን በአምበልነት የመራው አጥቂው የደደቢት አስራ ሁለተኛ ፈራሚ ነው።

ሁለተኛ ደደቢት የተቀላቀለው የመስመር ተጫዋቹ ክብሮም አስመላሽ ነው። ለተከታታይ ዓመታት መቐለ እና ስሑል ሽረ ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲያድጉ የቡድኖቹ አባል የነበረው ተጫዋቹ በቡድኑ ጥሩ አማራጭ ይፈጥራል ተብሎ ሲጠበቅ ለቋሚነትም ከከድር ሳልሕ ጋር ይፎካከራል። የትራንስ ኢትዮጵያ ሁለተኛ ቡድን ውጤት የሆነው የመስመር አማካዩ ከመድኃኔ ታደሰ ፣ ቢንያም ደበሳይ ፣ ዳዊት ዑቅበዝጊና ሙሴ ዮሃንስ ቀጥሎ ከትራንስ ኢትዮጵያ ታዳጊ ቡድን ወጥቶ ሰማያዊዎቹ የተቀላቀለ ስድስተኛ ተጫዋች ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ